የሰው ልጆች ላብን ማሽተት ለጭንቀት መድሃኒት ሊሆን ይችላል- ተመራማሪዎች
የስዊድን ጥናት ማዕከል የጭንቀት ህመም ያለባቸውን ሰዎች የሰዎችን ላብ አሽትተው ለውጥ ማሳየታቸውን ገልጿል
የማሰብ ችሎታ ስልጠናን ከሰዎች ላብ ጋር በማቀናጀት መስጠት ቢቻል የበለጠ ለውጥ ይመጣል ተብሏል፡፡
የሰው ልጆች ላብን ማሽተት ለጭንቀት መድሃኒት ሊሆን እንደሚችል ተገለጸ።
የአዕምሮ ህመም በዓለማችን እየተባባሰ መምጣቱን የተለያዩ ጥናቶች በመጠቆም ላይ ናቸው።
የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሰው ልጆችን ለአዕምሮ ህመም የሚዳርጉ መነሻዎችን እና መፍትሄዎችን በመጠቆም ላይም ናቸው።
የስዊድኑ ብሄራዊ ራስን የማጥፋት መከላከያ ጥናት ማዕከል ከዚሁ ጋር የተያያዘ ጥናቶችን ይፋ አድርጓል።
ማዕከሉ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች የሌሎች ሰዎችን የሰውነት ላብ ወይም ጠረን በማሽተት ለውጥ ማሳየታቸውን አስታውቋል።
ጭንቀት ከአእምሮ ህመሞች ውስጥ አንዱ ሲሆን የስዊድኑ ካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት ላለፉት ዓመታት ሲያካሂደው የቆየውን ጥናት ይፋ አድርጓል።
በኢንስቲትዩቱ የአዕምሮ ህመም አጥኚ የሖኑት ኤሊዛ ቪግና ጭንቀት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ልጆች ላብ ተሞክሮ ውጤት ማሳየቱን ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ የማሰብ ችሎታ ስልጠና እየወሰዱ ካሉ የጭንቀት ህመም ታማሚዎች ውስጥ የሰዎችን ላብ እንዲያሰቱ ከተደረጉት ውስጥ የ39 በመቶ ውጤታ አሳይተዋል ሲል ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
ኢንስቲትዩቱ እድሜያቸው ከ15 እስከ 35 የሆኑ 48 የጭንቀት ህመም ያለባቸውን ሴቶች ለይቷል።
በተቃራኒው ደግሞ የጭንቀት ህመም የሌለባቸውን በጎ ፈቃደኞች ለሶስት በመክፈል አስፈሪ ፣አዝናኝ እና የተለየ ስሜት የማይፈጥሩ ፊልሞችን እንዲያዩ ከተደረጉ በኋላ ላባቸው ወይም ሽታቸው ከእግር እና ከብብታቸው መወሰዱ ተገልጿል።
ከጤነኞቹ የተወሰደውን ላብ ጭንቀት ላለባቸው ህመምተኞች እንዲያሸቱ የተደረገ ሲሆን አስፈሪ አልያም አስቂኝ ፊልም ከተመለከቱ በጎ ፈቃደኞች የተገኘውን ላብ እንዲያሸቱ ከተደረጉት ውስጥ 39 በመቶዎቹ ከጭንቀት ህመም ማገገማቸውን በጥናቱ ላይ ተገልጿል።
እንዲሁም የተለየ ስሜት የማይፈጥሩ ፊልሞችን ከተመለከቱ ሰዎች የተገኘውን ላብ ካሸተቱ ህመምተኞች መካከል 17 በመቶዎቹ ለውጥ እንዳሳዩ ይሄው ጥናት አስታውቋል።
ይሁና ሁሉንም የላብ አይነቶች ባንድ ላይ በመቀላቀል ህምምተኞቹ እንዲያሸቱት ከተደረገ በኋላ የተገኘው ውጤት ተመሳሳይ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ እና አውሮፓ የአእምሮ ጤና ተመራማሪዎች በውጤቱ መደነቃቸውን ገልጸው ጉዳዩ የበለጠ ተጨማሪ ምርምር እንዲደረግበት አሳስበዋል።
የሰው ልጆች ላብ በተለይም በእጃችን በተለምዶ ብብት ሽታ እና የእግር ሽታ ከ300 በላይ ንጥረ ነገሮችን እንደሚያዝ ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል።
የጭንቀት ህመም ያለባቸው ታማሚዎች ይሄንን የሰው ልጆች ላብ ካሸተቱ በኋላ ለውጥ ያሳዩት በየትኛው ንጥረ ነገር እንደሆነ ጥናቱ አልመለሰም ተብሏል።