ከ100 አመት በላይ ለመኖር በተመራማሪዎች የተጠቆመ አስገራሚ ምክረሃሳብ
የአሜሪካው ቦስተን ዩኒቨርሲቲ 100 እና ከዚያ በላይ እድሜ ባላቸው አዛውንቶች ላይ ምርምር አድርጎ አዛውንቶቹ የሚጋሯቸውን ባህሪያት ይፋ አድርጓል
የጥናቱ ተሳታፊዎች በሙሉ በሽታን የመዋጋት አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱም ተመራማሪዎች የተለየ ምክረሃሳብ እንዲያቀርቡ አድርጓቸዋል
አለም የዜጎችን ህይወት ባጭሩ ለሚቀጩ በሽታዎች መድሃኒት ፍለጋ ስትኳትን፥ የቦስተን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ራሱ በሽታውን መስጠት እድሜን ዘለግ ያደርጋል የሚል አነጋጋሪ ጥናት ይፋ አድርጓል።
ዩኒቨርሲቲው በሰባት ከ100 እስከ 119 አመት እድሜ ባላቸው አዛውንቶች ላይ ያደረገውን ምርምር ይፋ አድርጓል።
ጥናቱ አዛውንቶቹ የሚጋሯቸውን ባህሪያት እና የዘረመል አይነት የዳሰሰ ነው።
እናም ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ጊዜ የገጠሟቸውን ህመሞች ተጋፍጠው ጠንካራ በሽታ የመከላከል አቅምን ማዳበራቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት ተመራማሪዎች።
የእድሜ ባለጠጋዎቹ ከህዳር በሽታ (ስፓኒሽ ፍሉ) እስከ ኮቪድ 19 ድረስ ያላለፉት ወረርሽኝ የለም።
ይህም ለተለያዩ ቫይረሶች ተጋልጦ በጠንካራ የመከላከል ብቃት ህመሞቹን ማሸነፍ እና የእድሜ ባለጠጋነት ያላቸውን ቁርኝት እንድንመለከት አድርጎናል ይላሉ የጥናቱ መሪ ጸሃፊ ፓውላ ሰባስቲያን።
የጥናት ቡድኑ በእድሜ ባለጠጎቹ ዘረመል ላይ ባደረጉት ምርምር ለበሽታ የማይበገሩ ህዋሳታቸው ብዛት ከፍተኛ መሆኑን ማረጋገጡን ለዴይሊ ሜል ገልጿል።
ለበርካታ አስርት አመታት ያካበበቱት ተፈጥሯዊ (በዘር የሚተላለፉ) እና ሰው ሰራሽ በሽታዎችን የማሸነፍ ብቃታቸው አሁን ላይ በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ እድሜ ከሚገኙ ወጣቶች ጋርም ተነጻጽሯል።
በዚህም የእድሜ ባለጠጎቹ ከ25 በላይ እድሜን የሚጨምሩ ህብረ በራሄ እንዳላቸው መረጋገጡንም ነው ሳባስቲያን የተናገሩት።
የእድሜ ጸጋ ከቤተሰብ በውርስ እንደሚተላለፍም የቦስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎቹ ጥናት አመላክቷል።
ላንሴት በተባለው ጆርናል ላይ የታተመው ጥናት ሰዎችን ለቫይረሶች በማጋለጥና ጠንካራ የመከላከል ብቃት እንዲያዳብሩ በማድረግ እድሜያቸውን ማዝለግ በተመለከተ በቀጣይ ተጨማሪ ምርምሮች ይደረጋሉ ብሏል።