ዩኤኢ እና እስራኤል ከተስማሙ ከዓመት በኋላ የመጀመሪያዋ እስራኤላዊ ህጻን በዱባይ ተወለደች
ሚያ የአብርሃም ስምምነት አንደኛ ዓመት በተከበረ በቀናት ውስጥ ነው የተወለደችው
‘ሚያ’ ትሰኛለች የተባለላት ህጻኗ በዱባይ የእስራኤል ቆንሱል ጄነራል አምባሳደር ኢላን ስታሮስታ ስቱልማን ልጅ ናት
ከታሪካዊው የአብርሃም ስምምነት ወዲህ የመጀመሪያ ናት የተባለላት እስራኤላዊት ህጻን በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ ተወለደች፡፡
ህጻኗ ‘ሚያ’ ትሰኛለች የተባለ ሲሆን በዱባይ የእስራኤል ቆንሱል ጄነራል አምባሳደር ኢላን ስታሮስታ ስቱልማን ልጅ ናት፡፡
ይህንንመ አምባሳደር ስቱልማን ደስታቸውን ባጋሩባቸው የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አስታውቀዋል፡፡
አምባሳደር ስቱልማን ሚያ ቆንጆ ባሏት ዱባይ ከተማ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ መወለዷን ባጋሩበት የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፋቸው “ተወዳጇ ልጃችን ሚያ ኢላን ስታሮስታ ስቱልማን እንኳን ወደዚህ ዓለም በሰላም መጣሽ…ከአብርሃም ስምምነት ወዲህ የተወለድሽ የመጀመሪያዋ እስራኤላዊት ህጻን…እንዴት ዐይነት ክብር ነው” ሲሉ ለጥፈዋል፡፡
ሚያ የአብርሃም ስምምነት አንደኛ ዓመት በተከበረ በቀናት ውስጥ ነው የተወለደችው፡፡ ይህ በዱባይ የተወለዱ ሌሎች እስራኤላውያን ቢኖሩም ሚያን ከአብርሃም ስምምነት በኋላ የተወደለች የመጀመሪያዋ እስራኤላዊት ህጻን አስብሏታል፡፡
ልክ የዛሬ ዓመት ወርሃ ነሃሴ ላይ ዩኤኢ እና እስራኤል የሁለትዮሽን ጨምሮ ሌሎች ግንኙነቶችን ለማድረግ ተስማምተው ኤምባሲዎቻቸውን እስከመክፈት ደርሰዋል፡፡
ይህ እርምጃ ባህሬይንን የመሳሰሉ ሌሎች የአረብ ሃገራት የተከተሉት ነበር፡፡
የሴት ልጃቸው መወለድ ከስምምነቱ አንደኛ ዓመት አከባበር ጋር የመገጣጠሙን አስደሳችነት የገለጹት አምባሳደር ስቱልማን “በንግድ እና በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ የተቀራረቡት ሃገራት አሁን ደግሞ በእውነተኛ ህይወት ተሳስረዋል፤ እዚህ መወለዷም ሃገራቱ እየገነቡት ላለው ጠንካራ ግንኙነት መታያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡