ልዩልዩ
ታሊባንን ሽሽት ወደ እንግሊዝ በመጓዝ ላይ የነበረች መንገደኛ በአውሮፕላን ውስጥ ወለደች
እንስቷ በበረራ አስተናጋጆች እርዳታ ሴት ልጅ መውለዷ ተነግሯል
ህጻኗ በ10 ሺህ ሜትር ከፍታ በኩዌት የአየር ክልል ላይ መወለዷም ተገልጿል
እንግሊዝ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ስር ከአሜሪካ እና ከሌሎች አባል አገራት ጋር ጦሯን ወደ አፍጋኒስታን ከላኩ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል።
ታሊባን አገሪቱን መቆጣጠሩን ተከትሎ በአፍጋኒስታን የእንግሊዝን ጦር በተለያዩ መንገዶች ሲረዱ የቆዩ አፍጋኒስታዊያን በአማጺው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ወደ አገሯ በማጓጓዝ ላይ ትገኛለች።
በዚህም ምክንያት በቱርክ አየር መንገድ አማካኝነት ወደ እንግሊዝ በመጓዝ ላይ ያለች አንዲት አፍጋኒስታዊ ሴት በጉዞ ላይ እያለች ሴት ልጅ መውለዷን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ሶማን ኑሪ የተሰኘችው ይህች የ26 ዓመት እንስት ከዱባይ ወደ እንግሊዟ በርሚንግሃም በመጓዝ ላይ እያለች በ10 ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ በኩዌት የአየር ክልል ላይ በበረራ አስተናጋጆች እርዳታ በሰላም መውለዷም ተጠቅሷል።
ህጻኗ እና እናቲቱ አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሀቫ የሚል ስም እንደወጣላትም ተገልጿል።
አውሮፕላኑ ለህጻኗ እና ለእናቷ ደህንነት ሲባል በኩዌት አርፎ የነበረ ቢሆንም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በረራውን ቀጥሏል ተብሏል።