3 ሺህ 518 እስረኞች ሲገደሉ፤ ተባባሪ ናቸው በሚል ወንጀል ነው እንደሚከሰሱም ተገልጿል
በጀርመን የናዚ ፖርቲ ዘብ ነበሩ የተባሉት የ100 ዓመት ግለሰብ አዛውንት ላይ ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑን የአውሮፓ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
ስማቸው ይፋ ያልተደረገው ግለሰቡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የጥበቃ ሰራተኛ ሆነው ማገልገላቸው ተገልጿል።
በዚህም መሰረት እ.እ.አ ከ 1942 እስከ 1945 ባለው ጊዜ 3 ሺህ 518 እስረኞች ሲገደሉ፤ ተባባሪ ናቸው በሚል ወንጀል ነው እንደሚከሰሱ የተገለጸው።
የ100 ዓመቱ አዛውንት ፍርድ ቤት ቆመው በቀን ሁለት ሰዓት ተኩል መከራከር እንደሚችሉ ባደረጉት የህክምና ምርመራ መረጋገጡን ዘ ዊክ የተሰኘው ድረ ገጽ ዘግቧል።
በጀርመን የናዚ ማጎሪያ ውስጥ ከአውሮፓውያኑ ከ 1936 እስከ1945 ባለው ጊዜ ውስጥ 200 ሺህ ሰዎች ታስረው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።
በረሀብ፣ በከባድ የጉልበት ስራ እና በበሽታ እንዲሁም በሞት ቅጣት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉም ይታወሳል።
አሁን ላይ የናዚ የማጎሪያ ካምፕ ዘበኛ የሆኑ ብዙ ግለሰቦች እንደሌሉ የተገለጸ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕጎች እነዚህን ግለሰቦች ካገኙ ግለሰቦች በቀጥታ በግድያ ስለመሳተፋቸው ማስረጃ ማቅረብ ሳይጠበቅባቸው መክሰስ እንደሚችሉ ሕግ ይፈቅድላቸዋል ተብሏል።
ባለፈው መጋቢት የ96 ዓመቱ የቀድሞ የናዚ ማጎሪያ የጥበቃ ሰራተኛ ተከሰው የነበረ ቢሆንም በችሎት መቆም እንደማይችሉ ተረጋግጦ እንደነበር መገናኛ ብዙኃን ጽፈዋል።