ጀርመን በናሚቢያ ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሟን አመነች
በዛሬዋ ናሚቢያ የተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶችን “በይፋ ጅምላ ጭፍጨፋ ብለን እንጠራቸዋለን”ንም ነው ሄኮ ማስ ያሉት
በርሊን ናሚቢያውያን በድርጊቱ ይቅር እንዲሏትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል በይፋ ጠይቃለች
ጀርመን ናሚቢያን ቅኝ በገዛችበት ወቅት ጅምላ ጭፍጨፋዎችን መፈጸሟን አመነች፡፡
በርሊን በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1904-08 ባሉት ዓመታት በደቡብ አፍሪካዊቷ ሃገር ዜጎች ላይ የፈጸመችውን ግድያ በጅምላ ጭፍጨፋነት ለመቀበል ስታቅማማ ቆይታለች፡፡
ሆኖም 5 ዓመታትን በወሰደ ንግግር ጭፍጨፋውን ስለመፈጸሟ አምና መቀበሏን ነው አሶሼትድ ፕሬስ የዘገበው፡፡
ይህን ተከትሎ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ለተለያዩ ልማቶች የሚውል የ1.3 ቢሊዬን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ተስማምታለችም ብሏል፡፡
ጄኔራል ሎታር ቮን ትሮታ በሄሬሮ ጎሳዎች የተነሳውን የጸረ ቅኝ ግዛት ተቃውሞ ለማርገብ በማሰብ ሙሉ የጎሳው አባላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በማዘዛቸው 65 ሺ ገደማ የጎሳው አባላት መጨፍጨፋቸውን እና በትንሹ 1 ሺ የናማ ጎሳ አባላት መገደላቸውን የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄኮ ማስ “ካለብን ታሪካዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነት አንጻር ናሚቢያውያን ይቅር እንዲሉን እንጠይቃለን” ብለዋል ባወጡት መግለጫ፡፡
ማስ በመግለጫቸው “ዓላማችን ተጎጂዎቹ የሚታወሱበትን እውነተኛ የእርቅ መንገድ መፈለግ ነው” ብለዋል፡፡
በዛሬዋ ናሚቢያ ቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶችን “በይፋ ጅምላ ጭፍጨፋ ብለን እንጠራቸዋለን”ም ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
በረሃማዋን ናሚቢያን በ1980ዎቹ በቅኝ ገዢነት የያዘችው ጀርመን እ.ኤ.አ በ2015 ለደቡብ አፍሪካ አስረክባት ነበር የወጣችው ሆኖም በ1990 ነጻነቷን አግኝታለች፡፡