ጀርመን ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የተዘረፉ ቅርሶችን ለናይጄሪያ እንደምትመልስ አስታወቀች
የመጀመሪያዎቹ ቅርሶች እ.ኤ.አ ከ2022 ጀምሮ እንደሚመለሱም ነው የተነገረው
ቅርሶቹ በቅኝ ግዛት ወቅት የተዘረፉ ናቸው ተብሏል
በቅኝ ግዛት ወቅት ከናይጄሪያ ተዘርፈው ወደ ጀርመን የተወሰዱ ቅርሶችን ልትመልስ መሆኗን ጀርመን አስታወቀች፡፡
የመጀመሪያዎቹን ቅርሶች እ.ኤ.አ በ2022 ለመመለስ እቅድ ስለመያዙም የሃገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
የጀርመን የባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የቅርስ ባለስልጣናት ከሰሞኑ ቅርሶቹ የሚመለሱበትን ሁኔታ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው በ1987 ከያኔዋ ቤኒን ከአሁኗ ናይጄሪያ በቅኝኝ ገዢው የብሪታኒያ ጦር ተዘርፈው የተወሰዱ የነሃስ ቅርሳቅርሶችንና የዝሆን ጥርሶችን ሌሎችን እንደሚመልሱ አስታውቀዋል፡፡
የተዘረፉት የነሃስ ቅርሳቅርሶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ በሙዚዬሞቿ በሰበሰበቻቸው ጀርመን ነው የሚገኙት፡፡
በበርሊን የብሄረሰቦች ሙዚየም ከሚገኙት 530 የቤኒን ታሪካዊ ቅርሶች ውስጥ 440 ያህሉ ከነሃስ የተሰሩ መሆናቸውን ከአሁን ቀደም የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።
ለዚህም ነው ጀርመን የሰበሰበቻቸውን ለመመለስ ቃል የገባችው፡፡ ቅርሶቹ የሚመለሱት በናይጄሪያ መንግስት ጥያቄ ነው፡፡
ሌሎችም ሃገራት የጀርመንን ፈለግ እንዲከተሉ ናይጄሪያውያን የቅርስ ባለስልጣናት እየጠየቁ ነው፡፡
“የወሰዷቸውን ሌሎችንም ቅርሶች ለባለቤቶቻቸው ሊመልሱ ይገባል” ብለዋል አስተያየታቸውን ለሲ.ኤን.ኤን የሰጡ አንድ የታሪክ ተመራማሪ፡፡
ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን በተቀራመቱበት ወቅት ዓይነተ ብዙ ቅርሶችን ዘርፈው ስለመውሰዳቸው ይነገራል፡፡
የቅርሶቹ መዘረፍ “በጦር አሸናፊነት የተገኘ የድል ዋንጫ አድርጎ ከመውሰድ የመጣ ነው” የሚሉ አንዳንድ የታሪክ ባለሙያዎች ታሪክና ባህልን ለማጥፋት፣ የእውቀት ጥገኝነትን (knowledge dependency) ለመፍጠር በማሰብ የተደረገ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ቅኝ ልትገዛ ያልቻለችው ኢትዮጵያም በዘረፋው ሰለባ ከሆኑ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ነች፡፡
በርካታ ቅርሶቿ በእንግሊዝ እንዲሁም በወራሪው የፋሺስት ጦር ወደተለያዩ የውጭ ሃገራት ተዘርፈው መወሰዳቸውም ይነገራል፡፡
በእግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን እና በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ሙዚዬሞችም ይገኛሉ፡፡
ቅርሶቹን ለማስመለስ አስመላሽ ኮሚቴ ጭምር ተቋቁሞ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
ያለፉትን 60 ዓመታት በእንግሊዝ ብሔራዊ የጦር ሙዝየም ውስጥ ያሳለፈው የአፄ ቴዎድሮስ ጉንጉን የራስ ጸጉር (ቁንዳላ) ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ የሚታወስ ነው።