ጀርመን ቅርሶቹን ለመመለስ ከቤኒን እና ናይጀሪያ ባለሰልጣናት ጋር ለረጅም ዓመታት ስትነጋገር ነበር ተብሏል
ጀርመን ከቅርስ ጋር በተገናኘ ያቋቋመችው ኮሚቴ እንዳስታወቀው በቅኝ ግዛት ዘመን ከቤኒን የተወሰዱ የመዳብ ቅርሶችን ለመመለስ ማሰቧን ገልጻለች።
የመዳብ ቅርሶቹ የተወሰዱት ቦታ በቅኝ ግዛት ዘመን ጊዜ በቤኒን ስር የነበረ ሲሆን ናይጀሪያ ነጻነቷን ከእንግሊዝ ከተቀዳጀች በኋላ ቅርሱ የተወሰደበት አካባቢ ወደ ናይጀሪያ ተካቷል።
በዚህም መሰረት ጀርመን የመዳብ ቅርሶቹን ለናይጀሪያ እንደምትሰጥ ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በወቅቱ ከቤኒን ግዛት የተወሰደው የመዳብ ቅርሶች አሁን ላይ በበርሊን የብሄረሰብ ሙዚየም ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጻል።
ጀርመን ቅርሶቹን ለመመለስ ከቤኒን እና ናይጀሪያ ባለሰልጣናት ጋር ለረጅም ዓመታት ስትነጋገር እንደቆየችን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄኮ ማስ ተናግረዋል።
ቅርሶቹ በቅኝ ግዛት ዘመን ጊዜ የተወሰዱ በመሆናቸው ለባለቤቶቹ መመለሳቸው ግድ ነው ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላለፉት ዓመታት በቤኒን ከሚገኘው የምዕራብ አፍሪካ ሙዚየም ኮርፖሬሽን ጋር ሲነጋገሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
በጀርመን መዲና የሚገኘው የበርሊን ብሄረሰቦች ሙዚየም 530 የቤኒን ታሪካዊ ቅርሶች እና እቃዎች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 440 የሚሆኑት ከመዳብ የተሰሩ እንደሆኑ ዘገባው ጠቁሟል።