ከሊባኖስ የተተኮሰ ሮኬት እስራኤል ውስጥ 11 ሰዎችን አቆሰለ
የአደጋ ጊዜ አገልግሎቱ እንደገለጸው ከሆነ ጉዳቱ የደረሰው ከተተኮሱት ሮኬቶች ውስጥ አንዱ በመኖሪያ ቤት ላይ በማረፉ ነው
በእስራኤል ኃይሎች እና በሄዝቦላ መካከል የሚደረገው ውጊያ ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ተጠናክሮ ቀጥሏል
በትናንትናው እለት ከሊባኖስ የተተኮሰ ሚሳይል በማዕከላዊ እስራኤል 11 ሰዎችን ማቁሰሉን የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት አስታውቋል።
የአደጋ ጊዜ አገልግሎቱ እንደገለጸው ከሆነ ጉዳቱ የደረሰው ከተተኮሱት ሮኬቶች ውስጥ አንዱ በመኖሪያ ቤት ላይ በማረፉ ነው።
በእስራኤል ኃይሎች እና በሄዝቦላ መካከል የሚደረገው ውጊያ ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን አሜሪካ በዚህ ሳምንት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ያደረገችው ጥረት የመሳካት ተስፋው መንምኗል።
ሮኬቱ በማዕከላዊ እስራኤል ባረፈበት ወቅት ሄዝቦላ በቴልአቪቭ ዳርቻ የሚገኝ ወታደራዊ ሰፈር ኢላማ ማድረጉን ገልጾ ነበር።
የእስራኤል አምቡባንስ አገልግሎት እንደገለጸው 11 ሰዎች በሮኬት ፍንጥርጣሪ ተጎድተዋል። ሮኬቶች እና ድሮኖች ከሊባኖስ በሚወነጨፉበት ወቅት የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደዎሎች ድምጽ በማዕከላዊ እስራኤል ሲሰማ ነበር ብሏል ጦሩ።
ባለፈው አርብ የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በዩኔስኮ የመዘገቡት የሮማን ከተማ ፍርስራሾች በሚገኙበት የቤካ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ ከደርዘን በላይ በሆኑ ከተሞች በእስራኤል የአየር ጥቃት 52 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት እንደገለጸው ባለፈው አርብ ታይሬ በተባለው አካባቢ በፈጸመው ጥቃት ሁለት የሄዝቦላ አዛዦችን ገድሏል። ሄዝቦላ በዚህ ጉዳይ አስተያየት አልሰጠም።
በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፍ የጀመረው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት በመክፈት 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ እና 1200 ሰዎችን ከገደለ ከአንድ ቀን በኋላ ነበር። ሄዝቦላ ወደ እስራኤል የሚተኩሰው የሀማስ አጋርነት ለማሳየት ነው።
የሀማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በወሰደችው መጠነሰፊ የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት 43ሺ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሀማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በሊባኖስ ቢያንስ 2897 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ደግሞ በሄዘቦላ ጥቃት እስራኤል ውስጥ እና በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባሉ ቦታቸው 71 ሰዎች ተገድለዋል።