አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ ናይም ቃሲም ማን ናቸው?
ሄዝቦላህን በመመስረቱ ሂደት የተሳተፉት ናይም ቃሲም ለውጭ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ቃለምልልስ በመስጠት ይታወቃሉ
ቃሲም የሀሰን ናስራላህን ግድያ የሚያረጋገጥ መግለጫ በመስጠትም ቀዳሚው ነበሩ
ሄዝቦላህ በዛሬው እለት አዲስ መሪውን ይፋ አድርጓል።
የሊባኖሱ ቡድን የሹራ ምክርቤት ሼክ ናይም ቃሲምን በመስከረም ወር በእስራኤል ጥቃት የተገደሉትን ሀሰን ናስራላህ እንዲተኩ መርጧቸዋል።
ናስራላህን ይተካሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ሃሽም ሰይፈዲን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ ነው ናይም ቃሲም የተመረጡት።
ሄዝቦላህን ከመመስረት ጀምሮ ከ30 አመታት በላይ በተለያዩ የሃላፊነት ስፍራዎች ያገለገሉት ቃሲም የናስራላህን ህልፈት በማረጋገጥ ቀዳሚው የቡድኑ አመራር ናቸው።
ሼክ ናይም ቃሲም ለ30 ደቂቃዎች በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ እስራኤል የሄዝቦላህን አመራሮች በመግደል የአመራር አቅሙን ለማዳከም ብትሞክርም “በጦርነቱ ቀድማ የምታለቅሰው ራሷ እንጂ ሄዝቦላህ አይደለም” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በናስራላህና ሌሎች አመራሮች ግድያም ሆነ ይህን ተከትሎ በተፈጸመው ድብደባ የሄዝቦላህ አቅም አልተነካም ያሉት ሼክ ናይም ቃሲም፥ በተደጋጋሚ መግለጫዎችን በመስጠትና ከውጭ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጋር ቃለምልልስ በማድረግ ይታወቃሉ።
ሼክ ናኢም ቃሲም ማን ናቸው?
በፈረንጆቹ 1953 በቤሩት ባስታ አል ታህታ በተባለ አካባቢ የተወለዱት ናይም ቃሲም፥ ቤተሰቦቻቸው ሽያ ሙስሊሞች ከሚበዙበት ደቡባዊ ሊባኖስ የተገኙ ናቸው።
ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ቃሲም በሄዝቦላህ ምስረታ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፥ በ1991 የወቅቱ የሄዝቦላህ መሪ አባስ አል ሙሳዊ ምክትላቸው እንዲሆኑ መርጠዋቸዋል።
አል ሙሳዊ በእስራኤል የሄሊኮፕተር ጥቃት በ1992 ከተገደሉ በኋላ ሀሰን ናስራላህ መሪነቱን ከተረከቡ በኋላም በሃላፊነታቸው ዘልቀዋል።
ናይም ቃሲም የፖለቲካ ተሳትፏቸውን አሃዱ ያሉት በፈረንጆቹ 1974 በተመሰረተው የሊባኖስ ሺያ አማል ንቅናቄ ውስጥ ነው።
የኢራን አብዮት መቀስቀስ በጀመረበት 1979 ግን ቃሲም የአማል ንቅናቄን ጥለው ወጥተዋል።
አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ ቡድኑን ለማቋቋም በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይም በንቃት የተሳተፉ ሲሆን፥ ሄዝቦላህ በ1982 በኢራን አብዮታዊ ዘብ አማካኝነት ሲመሰረትም ከመስራቾቹ ውስጥ አንዱ ነበሩ ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ቃሲም ሄዝቦላህ በ1992 የፓርላማ ምርጫ ሲሳተፍ ዋና አስተባባሪ እንደነበሩ መረጃዎች ያወሳሉ።
በ2005 የሄዝቦላህን ምስረታና ሌሎች ውስጣዊ ጉዳዮች ያሰፈሩበትን መጽሀፍ በማሳተምም ፈር ቀዳጅ ነበሩ።
ናስራላህ ከተገደሉ ወዲህ ሶስት ጊዜ በቴሌቪዥን መልዕክት ያስተላለፉት ናይም ቃሲም በሚሰጧቸው መግለጫዎችና ቃለመጠይቆች ምክንያት እንደ ሄዝቦላህ ቃልአቀባይ ይታያሉ።
ከ30 አመት በላይ በሄዝቦላህ እንቅስቃሴ ጉልህ ተሳትፎ ያላቸው አዲሱ መሪ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ዝግጁነታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።