በእስራኤል- ሄዝቦላህ ጦርነት ዙሪያ ያሉ አዳዲስ ክስተቶች ምንድን ናቸው?
ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የሮኬት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 7 ደረሰ
ባለፉት 24 ሰዓታት በእስረኤል የአየር ድብደባ የሞቱ ሊባኖሳውያን ቁጥር 45 ደርሷል
በእስራኤል እና በሊባኖሱ ሄዝበቦላህ መካከል የተጀመረው ጦርነት በአየር እና በእግረኛ ጦር መካከል በሚደረግ ውጊያ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ የቀጠለች ሲሆን፤ ሄዝቦላህ እስከዛሬ በቡድኑ ጥቅም ላይ ውለው የማያውቁ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ጭምር በመጠቀም እስራኤል ላይ ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል።
የሄዝቦላህ ጥቃት በእስራኤል ላይ
ሄዝቦላህ ተናንት በእስራኤል ላይ በሁለት ዙር በፈጸመው የሮኬት ጥቃት 7 ሰዎች መሞታውን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል በፈጸመው የሮኬት ጥቃት አንድ እስራኤላዊ አርሶ አደር እና ተቀጥረው ሲሰሩ አራት የውጭ ሀገር ዜጎችን ህይወት መቅጠፉ ነው የተገለተው
ሄዝቦላህ በሁለተኛ ዙር በፈጸመው የሮኬት ጥቃት አንዲት እናት ከወንድ ልጇ ጋር መሞቷ የተገለጸ ሲሆን፤ ሄዝቦላህ በያዝነው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ከፈጸመው ጥቃቶች ውስጥ አስከፊው መሆኑን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህም ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ሃይፋ አካባቢ በሚገኙ የእስራኤል ጦር ላይ በርካታ ሮኬቶችን መተኮሱን አረጋግጧል።
የእስራኤል ድብደባ በሊባኖስ
የእስራኤል ጦር ጄቶች አዳሩን በሊባሷ ዋና ከተማ ቤሩት ላይ ብቻ 10 የአየር ጥቃቶችን መፈጸሙ የተነገረ ሲሆን፤ ከሁለት የመኖሪያ መንደሮች ዜጎች ለቀው እንዲወጡም አሳስባች።
እስራኤል በቤሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ ቢያንስ 2 ሰዎች ሲሞቱ 4 ሰዎች ቆስለዋል ነው የተባለው።
እስራኤል በትናንትናው እለት በመላው ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በአጠቃላይ 45 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ የጤና ባለሙያዎች ናችው።
ከአየር ጥቃት በተጨማሪም በእግረኛ ጦር የሚደረገው ውጊያም የቀጠለ ሲሆን፤ ሄዝቦላህ ለሶስተኛ ተከታታይ ቀን በደቡባዊዋ የሊባኖስ ከተማ ኪያም ከእስራኤል ጦር ጋር ከፍተኛ ውጊያ መደረጉን ገልጿል።
ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ሊባኖስ ዘልቀው መግባታቸውን የሚያመላክት መሆኑ ተዘግቧል።
ባለፉት አምስት ሳምንታት ተፋፍሞ የቀጠለውን የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ጦርነት ለማስቆም እንዲሁም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ አለምአቀፋዊ ጥረቶች ቀጥለዋል።