“የእስራኤል መሪዎች በር እና መስኮቶቻቸውን ይጠብቁ” አያቶላ አሊ ሀሚኒ
የኢራን ጠቅለይ መሪ አያቶላ አሊ ሀሚኒ በእስራኤል ለተፈጸመው ጥቃት "አስከፊ ምላሽ" እንደሚሰጡ ዝተዋል
ሀሚኒ በኢራን ምድር በአሜሪካና እስራኤል አንዳች ጥቃት ቢፈጸም መካከለኛው ምስራቅን የሚያተራምስ ጦርነት ይከሰታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል
የኢራን ጠቅላይ መሪ እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን እና በአጋሮቿ ላይ ለሰነዘሩት ጥቃት "አስከፊ ምላሽ" እንደሚሰጡ ዛቱ።
አያቶላ አሊ ሀሚኒ ይህን ያሉት የኢራን ከፍተኛ አመራሮች እና ወታደራዊ አዛዦች ለጥቅምት 26ቱ የእስራኤል ጥቃት የበቀል እርምጃ እንደሚወሰድ በከፍተኛ ሁኔታ እያስጠነቀቁ በሚገኙበት ወቅት ነው።
ከሳምንት በፊት እስራኤል በኢራን 6 ከተሞች በ20 ቦታዎች እና በአራት ከፍተኛ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ አነጣጥራ በፈጸመችው ጥቃ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
የኢራን መንግስት ሚዲያ ባሰራጨው ቪድዮ ላይ ሀሚኒ “ጠላቶቻችን የጽዮናዊው አገዛዝም ይሁን አሜሪካ፣ በእርግጠኝነት በኢራን እና በኢራን ህዝብ ላይ ለፈጸሙት በደል አስከፊ ምላሽ ይጠብቃቸዋል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሀይማታዊ መሪው በማስጠንቀቂያቸው የአጸፋ ጥቃቱ መቼ እና የሚሸፍነው አካባቢ የት እንደሆነ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
ነገር ግን “የእስራኤል መሪዎቻቸው በር እና መስኮቶቻቸውን ይጠብቁ” የሚል ንግግር ማድረጋቸው ምናልባትም ቀጣዩ ጥቃት በግለሰቦች ላይ ሊያነጣጥር እንደሚችል ፍንጭ የሰጡበት ነው ሲል ኤፒ ዘግቧል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ በርካታ የጦር ሰፈሮች ያሏት አሜሪካ በስፍራው ወታደራዊ አቅሟን በማጠናከር ላይ ትገኛለች፡፡
በእስራኤል ውስጥ “ቲሀድ” የተባለውን ከፍተኛ ርቀት የሚሸፍነውን የአየር መቃወሚያ ስለመትከሏ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
በአረብያን ባህር አብርሀም ሊንከን አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከቦቿን ያሰማራችው ዋሽንግተን ተጨማሪ የውግያ መርከቦች ፣ ወታደሮች እና “ቢ-52” የረዥም ርቀት ቦምቦች ኢራንን እና አጋሮቿን ለመከላከል ወደ ቀጠናው እንደሚላኩ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጄነራል ፓት ራይደር ተናግረዋል፡፡
የእስራኤል እና ጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በቀጠናው በሚገኙ የኢራን አጋሮች ላይ ቴልአቪቭ በምትፈጽመው ጥቃት ኪሳራ እያደረሰች ትገኛለች፡፡
በጥቃቶቹ እስራኤል የቡድኖቹን አመራሮች ኢላማ ማድረጓ በመዋቅሮቻቸው ላይ መናጋት መፍጠሩ እየተነገረ ይገኛል፡፡
አያቶላ አሊ ሀሚኒ በዛሬው እለት ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በኋላ በኢራን ምድር ከአሜሪካም ሆነ እስራኤል አንዳች ጥቃት ቢፈጸም መካከለኛው ምስራቅን ሊያናጋ የሚችል ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡