ፖለቲካ
በጦርነቱ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች ከአንድ ወር በኋላ ይፈተናሉ ተባለ
ፈተናውን ያልወሰዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናቸውን ከጥር 24 እስከ 27 ይወስዳሉ ተብሏል
በሁለተኛ ዙር የሚሰጠውን ፈተና 58 ሺህ 936 ተማሪዎች እንደሚፈተኑ ተገልጿል
በ2013 ዓ.ም የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላልወሰዱ ተማሪዎች ከጥር 24 እስከ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ፈተናውን እንደሚወስዱ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ገልጿል።
በሁለተኛ ዙር የሚሰጠውን ፈተና 58 ሺህ 936 ተማሪዎች እንደሚወስዱም የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳን ጠቅሶ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
በፀጥታ ምክንያት ፈተና ያልወሰዱት በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ያሉ ተማሪዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ያለምንም ችግር መጠናቀቁን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ሁለተኛ ዙርም በሰላም እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ምክትል ሃላፊዉ መናገራቸውን ኢትቪ ዘግቧል፡፡
በሰሜን አትዮጵያ ባለፈው ጥቅምት ወር አንድ አመት ያስቆጠረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡