በጦርነቱ ምክንያት ኢንተርኔት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች በቅርቡ አገልግሎት ያገኛሉ ተባለ
ኢትዮቴሌኮም ዳግም አገልግቱን ለማስጀመር ከጸጥታ አካላት ጋር መነጋገር መጀመሩን ገልጿል
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ኢንተርኔን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል
ኢትዮቴሌኮም ዳግም አገልግሎት ለማስጀመር ከጸጥታ አካላት ጋር ንግግር መጀመሩን ገልጿል።
በአማራ ክልል ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ኢንተርኔት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎች አገልግሎት ለማስጀመር ከጸጥታ አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።
- በኢትዮጵያ የቴሌኮም ተደራሽነት 54.8 በመቶ ደርሷል- ኢትዮ ቴሌኮም
- በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሳተፍ ጨረታውን ያሸነፈው ኩባንያ የሚጠበቅበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አደረገ
የተቋሙ ቺፍ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት የተቋረጠውን አገልግሎት ዳግም ለማስጀመር ንግግር ተጀምሯል።
እንደ አቶ መሳይ ገለጻ አካባቢዎቹ በቅርቡ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ገልጸው ትክክለኛ ዕለቱን መናገር ግን እንደማይቻል ገልጸዋል ።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በብዙ ቦታዎች እንዲቋረጡ ሆኗል፡፡ ከኢንተርኔት በተጨማሪ የባንክ፤የመብራትና የውሃ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፡፡
ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት 24 አንድ አመት አስቆጥሯል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በርካታ ቦታዎች መቆጣጠር ቢችልም ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ጦሩን በትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
መንግስት ይህን ቢልም፤ ህወሓት የመንግስት ጦር እንዲወጣ ማድረጉን በወቅቱ ገልጾ ነበር፡፡ህወሓት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት በርካታ ቦታዎች መቆጣጠርም ችሎ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካውጀና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ በህወሃት ተይዘው የነበሩ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል ቦታዎች ነጻ ወጥተዋል፡፡
መንግስት የህወሓት ሀይሎችን በማሸነፍ ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች እንዲወጡ ማድረጉን ሲገልጽ ህወሓት በአንጻሩ “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን ይገልጻል፡፡
ከአንድ አመት በላይ ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሺዎች ሲገደሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡