ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን የገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ
ዞኑ ተፋናቃዮቹን ለመርዳት የክልል እና የፌደራል መንግስታት እንዲደግፉት ጠይቋል
ተፈናቃቹ በ12 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል
በአማራ ክልል ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን የገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረው ጦርነት በርካታ የሰብዓዊ መብት ጉዳቶች ማስተናገዱን የቀጠለ ሲሆን፤ የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል።
ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን በአማራ ክልል ብቻ 800 ሺህ ዜጎች በጦርነቱ መፈናቀላቸውን አል ዐይን ከአንድ ወር በፊት ክልሉን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ይታወሳል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ከዋግህምራ እና ሰሜን ወሎ በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደሴ እና አካባቢዋ ተጠልለው የነበሩ ዜጎች ጦርነቱን ሸሽተው በድጋሚ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ተፈናቅለዋል።
የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኀላፊ አቶ አበባው መሰለ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት፤ አስከ ትናንት ድረስ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን የመጡ ዜጎች ቁጥር 218 ሺህ 955 ናቸው።
ወደ ዞኑ የገቡ ተፈናቃዮችን ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አበባው፤ 12 ጊዜያዊ መጠለያዎችን በማዘጋጀት ለተፈናቃዮች ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።
በተፈናቃዮች ስምም ሌሎች አካላት ሰርገው እንዳይገቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ከጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አቶ አበባው ነግረውናል።
በጦርነቱ የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የሚናገሩት አቶ አበባው የክልሉ እና የፌደራል መንግስት ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ካትሪን ሱዚ ከተመራው የሰብዓዊ ድርጅቶች ልዑክ ጋር ዛሬ በባህርዳር መክረዋል።
ህውሓት ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ውይይቶች እና ጥሪ ቀርቦ እንደነበር ያስታወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በተግባር የተደገፈ ድጋፍ ግን የውይይቱን ያክል አልተገኘም ብለዋል።
የተ.መ.ድ. የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ በበኩላቸው በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እንደሚሠራ ተናግረዋል።