በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ከ400ሺ በላይ ተፈናቃዮች በሰሜን ሽዋ ዞን እንደሚገኙ ተገለጸ
ዞኑ ተፈናቃዮቹ በ10 መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ገልጿል
በዞኑ ዋና ከተማ ደብረብርሃን ብቻ ከ200 እስከ 250ሺ ተፈናቃዮች ተጠልልው እንደሚገኙ ዞኑ አስታውቋል
በፌደራል መንግስትና በህወሃት ሃይሎች መካከል ያለው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት ከገባ ከ8 ወራት በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያውጅም፣ በአዋጁ አልገዛም ያለው ህወሓት ወደ አፋርና አማራ ክልል በመግባቱ ጦርነቱ እስካሁን ቀጥሏል፡፡ ህወሃትም ወደ አፋርና አማራ ክልል በመንቀሳቀስ ጥቃት መክፈቱን በጊዜው መግለጹ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በሁለቱ ክልሎች ጥቃት መክፈቱን የአፋርና አማራ ክልሎች ገልጸው፤ጥቃቱን ለመቀልበስ የክተት አዋጅ ማወጃቸውም ይታወሳል፡፡
በሰሜን ወሎ፣ በዋግኽምር፣ በሰሜን ሸዋና በአፋር ክልል የተለያዩ ዞኖች በነበረው ጦርነት ምክንያት እስካሁን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ለስደት ተዳርገዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ከተሞች ደሴና ኮምቦልቻም በህወሃት መያዛቸውን ተከትሎ ከ400 ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃንን ጨምሮ በተለያዩ የዞኑ ከተሞች ተጠልለው እንደሚገኙ መንግስት ገልጿል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ይንገሱ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት አሁን ላይ በዞኑ 441 ሺ 625 ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ተፈናቃዮችም በዞኑ በሚገኙ 16 ወረዳዎች ተጠግተው እንደሚኖሩ የተገለጸ ሲሆን አንጎለላ ጠራ፣ ግሼ ራቤል፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ አንኮበር፣ ምንጃር፣ መርሐቤቴ፣ ሚዳ ወረሞ እና ሌሎችም ቦታዎች በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉባቸው አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡
በደብረ ብርሃን ብቻ ከ 200ሺ እስከ 250 ሺ ተፈናቃዮች እንዳሉ ያነሱት ቡድን መሪው ከዚህ ውስጥ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የገቡት 24 ሺ ብቻ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ደረጀ ተፈናቃዮቹ በ10 መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ የገለጹ ሰሆን በርካቶቹ ግን በግለሰቦች ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ በደብረብርሃን ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል የተወሰኑትን አነጋግሯል፡፡ ከሰሜን ወሎ መርሳ ከተማ እንዲሁም ከሰሜን ሸዋ ሸዋሮቢት ከተማ መምጣታቸውን የገለጹ ሁለት ተፈናቃዮች ጦርነቱ ህይወታቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ እየመሩት ያለው ህይወት አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው መመለስን አሁንም ተስፋ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ አጠናቆ እነርሱንም ወደመኖሪያ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ተስፋ አድርገዋል፡፡
በተፈናቃዮች መጠለያ እግር ከኳስ ሲጫወቱ ያገኘናቸው ታዳጊዎችም ጦርነቱ ካፈናቀላቸው ዜጎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ታዳጊዎቹ መንግስት በአስኳይ ወደቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል፡፡
ከአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የገለጹት ተፈናቃየቹ ሌሎች እርዳታ ሰጭ ድርጅቶችም ወደ አካባቢው በመምጣት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡት ታዳጊዎች በአካባቢያቸው ያለው ድባብ እንደናፈቃቸው እና አሁንም ቶሎ ወደመጡበት መመለስ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች ጦርነት እየተካሄደ ሲሆን ይህ ተጠናቆ ማየት የተፈናቃቹ ተስፋ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ “ አካባቢያችን ባለው ጦርነት ተፈናቅለን ነው የመጣነው፤ አሁን ወደመጣንበት መመለስ እንፈልጋን” ሲሉም ተፈናቃዮቹ ገልጸዋል፡፡
ከተለያዩ ቦታዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ ወደየአካባቢያቸው እንደሚመለሱ ተስፋ አድርገዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ይንገሱ በመጠለያ ውስጥ ላሉት ተፈናቃዮች ድጋፍ ቢደረግም የተሟላ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልእክት፤ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር ስለሆነ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሩ አቅርበዋል፡፡