ለ12 ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው ይህ አልኮል የአናናስ ጣዕም ያለው ጅን ነው ተብሏል
በኡጋንዳ የአናናስ ጣዕም ያለው የጅን አልኮል የጠጡ 12 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ።
በምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ ሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ የአናናስ ጣዕም ያለው አልኮል የጠጡ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ ዘግቧል።
ማዲ ኦኮሎ ቡተባለው ግዛት ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ እለት የአናናስ ጣዕም ያለው የጅን አልኮል መጠጥ የወሰዱ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
ሀገር በቀል በሆነ የአልኮል መጠጥ አምራች ኩባንያ እንደተመረተ የተገለጸው ይሄንን አልኮል የጠጡ ሌሎች ዜጎችም ህክምና ላይ ናቸው ተብሏል።
አምስት የዚህ አልኮል ምርቶችም ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ካምፓላ ብሄራዊ ቤተሙከራ ማዕከል ተልኮ ውጤቱ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ የአናናስ ጣዕም ባለው የጅን አልኮል መጠጥ ውጫዊ ክፍል ላይ ውሀ፣ እና ሌሎችም ግብዓቶች እንዳሉበት ተጽፏል ተብሏል።
ከአልኮሉ ክስተት ጋር ተያይዞም አራት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ተይዘው ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን አልኮል አምራቹ ድርጅት እንደተዘጋ ዘገባው ጠቁሟል።
በኡጋንዳ ከአልኮል መጠጥ መመረዝ ጋር ተያይዞ የዜጎች መሞት የተለመደ ሲሆን በፈረንጆቹ 2010 ላይ 80 ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ መሞታቸው ይታወሳል።