ሀገራቱ እገዳውን የጣሉት በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ነው ብለዋል
ጋና እና ኡጋንዳ የጥራጥሬ ምርቶች ከሀገራቸው እንዳይወጣ አገዱ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ሶስት ወራት አልፎታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት የዩክሬን ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞችን ጨምሮ የንግድ ማሳለጫ ወደቦች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።
የዚህ ጦርነት ዳፋ ከሁለቱ ሀገራት ባለፈ ለዓለም የተረፈ ሲሆን የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ ምክንያት ሆኗል።
በዚህ የዋጋ መና ስጋት የገባቸው የዓለም ሀገራት ምርቶቻቸው ወደ ውጭ ሀገራት እንዳይላኩ እገዳዎችን በመጣል ላይ ሲሆኑ ህንድ እና ሀንጋሪ አስቀድመው የወሰኑ ሀገራት ናው።
አሁን ደግሞ አፍሪካዊያኑ ጋና እና ኡጋንዳ ጥራጥሬ እና ሌሎች ምግቦች ከሀገር ውጪ እንዳይሸጡ እገዳ መጣላቸው ተገልጿል።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ከዚህ በፊት ወደ ጎረቤት ሀገራት ትልካቸው የነበሩ በቆሎ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች ጥራጥሬዎች እንዳይላኩ እገዳ መጣሏን አስታውቃለች።
ይሁንና የጋና ገበሬዎች በመንግስት ውሳኔ ደስተኛ ያለሆኑ ሲሆን የምርት ዋጋ ሊቀንስ ይችላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል ተብሏል።
ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ኡጋንዳ በበኩሏ ወደ ውጪ ሀገራት በሚላኩ የግብርና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ግብር የጣለች ሲሆን ዋና አላማውም ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች ከሀገር እንዳይወጡ ለማድረግ ነው።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ በምግብ እና ሸቀጣሸቀጦች ላይ የዋጋ መናር ቢያጋጥም መንግስታቸው ጣልቃ እንደማይገባ መናገራቸው ይታወሳል።
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ምግብ ነክ ምርቶች ወደ ሀገራት እንዳይወጡ የሚደረጉ እገዳዎች እንዳይጣሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።