ለኡጋንዳ “ማንም ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግረን አይችልም” ሲሉ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ተናገሩ
በተመድ የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ዩጋንዳን እየጎበኙ ነው
ሩሲያን ለማውገዝ በተጠራው የተመድ ጉባኤ ላይ ኡጋንዳ ድምጸ ተዓቅቦ ማድረጓ ይታወሳል
ለኡጋንዳ “ማንም ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግረን አይችልም” ሲሉ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ተናገሩ።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ ባለፈው ሳምንት በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ መጎብኘቷ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ዩጋንዳን በመጎብኘት ላይ ናቸው።
የሁለቱ የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ዩጋንዳን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ጥያቄ የቀረበላቸው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮሪ ካጉታ ሙሴቪኒ "ማንም ምን ማድረግ እንዳለብን ሊመራን አይችልም" ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ "ካምፓላን መጎብኘት ከፈለጉ በራችን ክፍት ነው፣ ሁሌም እንኳን ደህና መጣሽ ብለን እንቀበላታለን" ያሉት ፕሬዝዳንቱ ነገር ግን ምን ማድረግ እንዳለብን ወደ መናገር ከገቡ ግን "ማንም ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግረን አይችልም" እላታለሁ ብለዋል።
እርዳታ ከምዕራባዊያን ከመጣልን እንቀበላለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ በእርዳታ ስም እጃችንን ለመጠምዘዝ ከሞከሩ ግን ኡጋንዳ ያለ እርዳታም እንደምትኖር እናሳያለን ማለታቸው ተገልጿል።
እስካሁን ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ዩጋንዳ ላይ ተጽዕኖ ለማድረስ የሞከረ ሀገር እንደሌለም ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ አክለዋል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት እና ጉዳዩን ለማውገዝ በተካሄደው የተመድ ስብሰባ ላይ 16 የአፍሪካ ሀገራት ድምጸ ተዓቅቦ ያደረጉ ሲሆን ኡጋንዳ አንዷ ነበረች።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ጦርነት ኡጋንዳ እንደምትረዳ እና የወቅቱ ፍላጎት እና ሁነት ምን እንደሆነ እንረዳለንም ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።