ኡጋንዳ ስዋሂሊ ቋንቋን የስራ ቋንቋዋ እንዲሆን ወሰነች
ስዋህሊ ቋንቋ ከ200 ሚሊዮን በላይ ተናጋሪዎች ያሉት አፍሪካዊ ቋንቋ ነው
የአፍሪካ ህብረት ስዋህሊ ቋንቋን የሕብረቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል
ኡጋንዳ ስዋሂሊ ቋንቋን የስራ ቋንቋዋ እንዲሆን ወሰነች፡፡
ስዋሂሊ የተሰኘው ብሄር ቋንቋ እንደሆነ የሚነገርለት ስዋሂሊ በኬንያ እና ታንዛኒያ ድንበር አካባቢ በሚኖሩ ህዝቦች በብዛት ይነገር ነበር፡፡
የቋንቋው ተናጋሪዎች በየጊዜው እያደገ መጥቶ አሁን ላይ ከ200 ሚሊዮን በላይ ተናጋሪዎችን አፍርቷል፡፡
ቋንቋው በኬንያ፣ታንዛኒያ፣ቡሩንዲ፣ሩዋንዳ ኡጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ብዙ ተናጋሪ ህዝቦች ያሉት ሲሆን በኢትዮጵያም በኬንያ ድንበር ዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ይናገሩታል፡፡
ኬንያ እና ታንዛኒያ ይፋዊ የስራ ቋንቋቸው ያደረጉት ሲሆን አሁን ደግሞ ኡጋንዳ ስዋሂሊን የስራ ቋንቋዋ እንዲሆን መወሰኗን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኡጋንዳ ካቢኔ እንደወሰነው ከሆነ ስዋሂሊ ቋንቋ ከስራ ቋንቋነት ባለፈ በአንደኛ ደረጃ እነቃ ሁለተ ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥም ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል፡፡
የባንቱ ቋንቋ ቤተሰብ እንደሆነ የሚነገርለት ስዋሂሊ ቋንቋ በዓለም ላይ ብዙ ተናጋሪዎች ካሏቸው 10 ቋንቋዎች መካከል አንዱ ሲሆን በየጊዜው የተናጋሪዎች ቁጥር በማደግ ላይ ይገኛል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚነገረው ይህ አፍሪካዊ ቋንቋ በርካታ ሀገራት ውስጥ ቋንቋውን ለመጠቀም ፍላጎት በማሳየት ለይ ሲሆኑ ደብባዊ እና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጥረቶችን በማድረግ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
ደቡብ አፍሪካ እና ጋና ስዋሂሊ ቋንቋ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላሉ ተማሪዎች እንዲሰጥ የወሰኑ ሲሆን ኢትዮጵያም ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፡፡
ለአብነትም የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የስዋሂሊ ቋንቋን ለማስተማር በጥረት ላይ መሆኑን ከዚህ በፊት የገለጸ ሲሆን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ወይም ኦቢኤን በስዋሂሊ ቋንቋ ስርጭት ጀምሯል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ባሳለፍነው የካቲት በአዲስ አበባ ባካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ስዋሂሊ ቋንቋን የህብረቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡
ከአፍሪካ ህብረት አባል ከሆኑ 54 ሀገራት መካከል 24ቱ ሀገራት የመጀመሪያ የስራ ቋንቋቸው እንግሊዘኛ ሲሆን 21 ሀገራት ደግሞ ፈረንሳይኛን የስራ ቋንቋቸው ሲያደርጉ አረብኛ፣ስፓኒሽ እና ፖርቹጋል ቋንቋዎችም የብዙ አፍሪካ ሀገራት ይፋዊ የስራ ቋንቋዎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡