"ህወሓትን በማፍረስ አንሳተፍም" ያሉ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ
የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጌታቸውም ሆኑ ህወሓት የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ አልተቀበሉትም።
ህወሓት፣ ከምዝገባ ጋር በተያያዘ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ያለው ችግር ሳይፈታ ጉባኤ ለማካሄድ ማቀዱም ተገቢ አይደለም ብለዋል
"ህወሓትን በማፍረስ አንሳተፍም" ያሉ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በፓርቲው ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።
በትግራይ ቴሌቪዥን በተላለፈው እኝህ አባላት ባወጡት የጋራ መግለጫ "ህወሓትን ለማፍረስ በሚደረግ ጉባኤ አንሳተፍም" ብለዋል።
መግለጫውን ያወጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጌታቸው ረዳ፣በየነ መክሩ፣ክንደያ ገብረህይወት፣ ሀጎስ ጎደፋይ፣ሰብለ ካህሳይ፣ ብርሃን ገብረየሱስ፣ ሰለሞን ማዓሾ፣ ሺሻይ መረሳ፣ ሀብቱ ኪሮስ፣ ረዳኢ ሀለፎም፣ ነጋ አሰፋ፣ ገብረህይወት ገብረእግዝሄር፣ ሩፋኤል ሽፈሬ፣ ርስቁ አለማው ናቸው።
የተወሰነ የህወሓት ቡድን ጉባኤውን ከህወሓት አሰራር ውጭ ለማካሄደ በማሰቡ ምክንያት ላለመሳተፍ አቋም ይዘናል ያሉት አባላቱ የታቀደው ጉባኤ ደቡባዊ እና ምዕራብ ትግራይን ጨምሮ የማያሳትፋቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
አባላቱ እንዳሉት ህወሓት፣ ከምዝገባ ጋር በተያያዘ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ያለው ችግር ሳይፈታ ጉባኤ ለማካሄድ ማቀዱም ተገቢ አይደለም።
ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሰነምግባር ማሻሻያ አዋጅ መሰረት፣ ህወሓት "በልዩ ሁኔታ" በፓርቲነት እንዲመዘገብ ወሳኔ አስተላልፏል። ህወሓት የጠየቀው ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ቢሆንም ቦርዱ በተሻሻለው አዋጁ በልዩ ሁኔታ ከመመዝገብ ውጭ ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል አሰራር አለመኖሩን ገልጿል።
የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጌታቸውም ሆኑ ህወሓት እንደ ድርጅት የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ አልተቀበሉትም።
አባላቱ እንደገለጹት በዚህ ሁኔታ ወደ ጉባኤው መግባት ህወሓትን እና የትግራይን ህዝብ ቀውስ የሚያስገባ ነው።አቶ ጌታቸው በድርጁቱ ጉባኤ እንደማይሳተፉ የገለጹት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከህወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ራሳቸውን ማግለላቸውን ባሳወቁበት ደብዳቤ ምን አሉ?
አቶ ጌታቸው በጉባኤው እንደማይሳተፉ ያስታወቁት ነሃሴ 2፣2016 ዓ.ም ለህወሓት ሊቀ መንብር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) እና ለፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ መንበረር አቶ ተክለብርሃን አርአያ በጻፉት ደብዳቤ ነው።
“የህወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ከ3 ዓመታት በፊት መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በአንድአንድ የድርጅቱ አመራሮች ደርቅና ሳይካሄድ ቆይቷል” ሲሉ አቶ ጌታቸው በዚሁ ደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል።