ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾሙ
አቶ ጌታቸው አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈፃሚ አካል የመምራት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል
ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ለጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንትነት እጩ አድረጎ መምረጡ ይታወሳል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው መሾማቸው ተገለፀ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀፅ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፤ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ግጭትን ለማቆም በፕሪቶርያ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምነት አንቀጽ 10(1) መሠረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም በማስፈለጉ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጋቢት 9፣2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ “የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብን መጽደቁ ይታወሳል።
- ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ለጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንትነት እጩ አድረጎ መረጠ
- በትግራይ ጊዜያዊ መንግስት በአጭር ጊዜ እንደሚቋቋም የህወሓት ቃል አቀባይ ተናገሩ
በዚሁ ደንብ አንቀጽ 3(2) መሠረት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በከልሎ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ውክልና የሚያረጋገጥ እና አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈፃሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
ህወሓት መጋቢት 8 ቀን 2015 ባካሄደው ስብሰባው አቶ ጌታቸው ረዳን ለጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንትነት እጩ አድረጎ መምረጡ ይታወሳል።
41 አባላት ያሉት የህወሓት መአከላዊ ኮሚቴ አቶ ጌታቸውን የመረጠው ሰባት እጩዎችን ለምርጫ ካቀረበ በኋላ ነው ተብሏል።
ማአከላዊ ኮሚቴው በሰጠው ድምጽ አቶ ጌታቸው ረዳ በ18 ድምጽ አንደኛ እንዲሁም ፍስሃ ሃፍተጽዮን በ17 ድምጽ ሁለተኛ ሆነው ተመርጠዋል።