አቶ ጌታቸው ረዳ ከህወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ራሳቸውን ማግለላቸውን ባሳወቁበት ደብዳቤ ምን አሉ?
አቶ ጌታቸው፤ “አሁን እየተደረገ ስላለው ቅጥ ያጣ እንቅስቃሴ እኔም ሆነ የማዕካለዊ ኮሚቴውአናውቀውም” ብለዋል
አቶ ጌታቸው ጉባዔው “ከ3 ዓመታት በፊት መካሄድ የነበረበት ቢሆንም አንድ አንድ የድርጅቱ አመራሮች ደርቅና ሳይካሄድ ቆይቷል” ብለዋል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትና የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ከህወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ነሃሴ 2 2016 ዓ.ም ለህወሓት ሊቀ መንብር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) እና ለፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ መንበረር አቶ ተክለብርሃን አርአያ በጻፉት ደብዳቤ ነው ራሳቸውን ከጉባዔው መግለላቸውን ያስታወቁት።
የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ በደበዳቤያቸው “የህወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ከ3 ዓመታት በፊት መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በአንድ አንድ የድርጅቱ አመራሮች ደርቅና ሳይካሄድ ቆይቷል” ብለዋል።
ከወራት በፊት ጉባዔውን ለማካሄድ የተመረጠው የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ፤ በሂደት ከድርጅቱ አሰራር እና እሴት ውጪ በጥቂት ሰዎች ስለታፈነ ማዕካለዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ከጉባዔው ራሱን ማግለሉን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፤ በዞን እና በወረዳ ደረጃ ተመሳሳይ ብዙ አካላት ራሳቸውን እያገለሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
“የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ጭምር ድርጅታዊ ጉባዔው መቼ እና እንዴት መካሄድ እንዳለበት አንድ አይነት አረዳድ የለውም” ብለዋል አቶ ጌታቸው።
“መሬት ያለው ቅጥ ያጣ እንቅስቃሴ መጨረሻ ላይ ድርጅቱን እና ህዝባችንን ወደ ከፋ አደጋ እንደሚያስገባ ግልጽ እየሆነ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ “አሁን እየተደረገ ስላለው ቅጥ ያጣ እንቅስቃሴ እኔም ሆነ የማዕካለዊ ኮሚቴውአናውቀውም” ሲሉም ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው “ስለ ጉባዔው አካሄድ፣ ዴሞክራሲያዊነት እና ህጋዊነት ወደ አንድ መግባባት ሳይደረስ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ያሳላሳፈበት እና የማያውቀው የምዝገባ እንቅስቃሴ እያካሄደ ያለው አካል እንደለ ተረድተናል” ብለዋል።
“ይህ አካል የድርጅታችንን አሰራርና አደረጃጀት ከነአካቴው ለማጥፋትና የራሱን ፍላጎት ለማረጋገጥ ሲል ድርጅታችን ሊወጣው ወደማይችለው አደጋ የሚያስገባ መንገድ ላይ ነው እየተንቀሰቃሰ ያለው” ሲሉም ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው “ህገ ወጥ” ያሉት ቡድን ማዕካለዊ ኮሚቴው ለምዝገባ ብሎ ያልፈረመበት የተጭበረበረ ሰነድ አያይዞ በአዲሱ አዋጅ መሰረት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ስለማቅረቡም ጠቅሰዋል።
“ይህ አካሄድ ተራ ስህተት ሳይሆን፤ ድርጅቱን ለማፍረስ እና የትግራይ ህዝብን የህልውና ትግል ከንቱ ለማድረግ ሆን ተብሎ እየተሰራ ያለ የጥፋት ቡድን እንቅስቃሴ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
ስለሆነም “የድርጅቱን እውቅና ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የገባ የእውቅና ጥያቄ ይሁን፤ በህወሓት ስም እየተደረገ ያለ የጉባዔ እንቅሰቃሴ ሁሉ፤ ፓርቲውን የማይወክሉ የአንድ ቡድን ህጋዊ ያልሆነ እነቅስቃሴ ስለሆነ በጭራሽ የማልቀበለው መሆኔን ለማሳወቅ እወዳለሁ” ብለዋል።
እየተደረገ ያለው ስርዓት አልባ እንቅስቃሴ ድርጅቱን የሚያፈርስ ስለሆነ ይህንን ህገ ወጥ እቅስቃሴ ለማስቆም በጽናት እንደሚታገሉም አስታውቀዋል።
“ህወሓት የሚድነው እኛ የድርጅቱ አባላት እና ህዝቡ በአጠቃላይ በምናደርገው ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ እንጂ የድርጅቱ የአሰራር መመሪያ እና አሴት እየተጣሰ በሚደረግ ስርዓት አልባ ቡድን እንቅስቃሴ እንደላሆነ ለማሳወቅ እወዳለሁ” ብለዋል።
አቶ ጌታቸው እኔን ጨምሮ የየቁጥጥር ኮሚሽን እና በርካታ የድርጀቱ ከፍተኛ አመራር ያነሷቸው ጥያቄዎች በአግባቡ እስኪመለሱ በአንድ ቡድን በተዘጋጀ ጉባዔ ይሁን የድርጅቱ የከፍተኛ አመራሮች ውሳኔ የጣሰ የምዝገባ ሂደት ላይ የማልሳተፍ መሆኔን ለማሳወቅ እወዳለሁ” ብለዋል።