“የተጋረጡብንን ችግሮች አብረን ተባብረን መፍታት አለብን”- ፕሬዘዳንት ሳህለ ወርቅ ዘዉዴ
14ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ አበባ ስታዲየም ዛሬ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. “ህገመንግስታዊ ቃልኪዳናችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡
በክብረበዓሉ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተሳተፉ ሲሆን የየብሄሩ ልዑካን አባላት የየአካባቢያቸውን ጭፈራ፣ አለባበስ፣ የተለያዩ ቁሶች እና ሌሎች መገለጫዎቻቸውን አሳይተዋል፡፡
የዛሬው በዓል የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት ሳህለ ወርቅ ዘዉዴ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሰት ባለስልጣናት በተገኙበት ነው በአዲስ አበባ ስቴዲየም የተከበረው፡፡
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዘዳንት ሳህለ ወርቅ ዘዉዴ ያለፈው 13ኛው የብሔር ብሐየረሰቦች ቀን ከተከበረ ወዲህ ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን ማሳለፏን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ስለሀገራችን ስናነሳ የሚለያዩንን እና ችግሮቻችንን ብቻ ከማውራት መፍትሔዎችንም በመሰንዘር የሰከነ ሁኔታን መፍጠር አለብን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዓሉ የተለያዩ ባህሎቻችንን እና አኗኗራችንን የበለጠ እንዲታወቁ በማድረግ አንድነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል ያሉት ፕሬዝዳንቷ፣ እንደሀገርና ህዝብ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሰራነውን እና ወደፊት መስራት ያለብንን የቤት ስራ ለመገምገምም ይረዳናል ብለዋል፡፡
ሁሉም ነገር የሚያምረው እና እንደሰው ክብር ኖሮን መኖር የምንችለው ኢትዮጵያችን እስከኖረች ብቻ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ሁላችንም አንድነታችንን ጠብቀን በኢትዮጵያችን ህልውና ሳንደራደር የጋራ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ እስከተነሳን ድረስ የሚያቆመን ኃይል የለም ብለዋል፡፡
“የተጋረጡብንን ችግሮች አብረን ተባብረን ከመፍታት ውጭ ሌላ ምርጫ የለንም፡፡ ችግሮቻችንን በጋራ በመወያየት፣ በመደማመጥ… ካልተስማማን ላለመስማማት በመስማማት መፍታት ይኖርብናል፤ በዚህም ብቸኛ የጋራ ቤታችንን እንገንባ፡፡” በማለትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ባደረጉት ንግግር ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በአል “ከአንደነት ይልቅ ልዩነትን ያጎላል” መባሉ በአሉን ለማሳነስ ያለመና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ አመለካካት ነዉ ብለዋል፡፡
የህገ-መግስቱንና የበአሉን አስፈላጊነት በአግባቡ ካልተረዳን ስጋት እንደሆነ ሁሉ በአግባቡ ከተያዘ ደግሞ የአንድነት ማጠናከሪያ ይሆናልም ብለዋል ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን በመገንባት የዜጎች መብት እንዲከበር የጀመርነው መንገድ እንዲሳካ ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ በበዓሉ መክፈቻ ላይ ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ በጋራ እንዲወስን ለማድረግ የተጀመረወን የለውጥ ጉዞ በፍጥነት ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በአሉን በማስመልከት በዋዜማው ህዳር 28 የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአሉ “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተዛመዱ፣ የተጋመዱ፣ የተወራረሱ፣የተሠናሠሉ፣ መሆናቸውንም የምናይበት ነው” ብለዋል፡፡
ላለፉት አመታት ሀገራዊ አንድነት ከብሔር ማንነት ጋር ሆን ተብሎ እንዲጣላ ተሠርቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አንዳንዶች ከጠቅላላዋ ኢትዮጵያ እንዲጠቀሙ፤ብዙዎች ግን ከአካባቢያቸው ብቻ እንዲጠቀሙ ሲሠራ ኖሯል፣ አሁን ግን ያ ጊዜ አብቅቷል፣ ሲሉ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን በዓል ስናከብር ወደ ቀደመው አሐዳዊነትም ሆነ ወደ እጅ አዙር አሐዳዊነት ዳግም እንደማንመለስ እያረጋገጥን ነው ካሉ በኋላ የሀገሪቱን ፌዴራላዊ ሥርዓት ስሙን ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ አተገባበሩን በትግላችን እንደጨበጥነው እያረጋገጥንም ነው በዓሉን ምናከብረው ብለዋል፡፡