በኤርትራ የኮሉሊ ፖታሽ ፕሮጄክት 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈሰስ ማድረጉን የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (AFC) አስታወቀ፡፡
በአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የተመደበው ገንዘብ በደናኪል ዝቅተኛ ስፍራዎች ላይ ለሚጀመረው ግዙፍ ፖታሽዬም ሰልፌት የማምረት ፕሮጄክት ግንባታ የሚውል ነው ብሏል የቢዝነስ ዋዬር ድረ ገጽ፡፡
ፕሮጄክቱ ኤርትራ አላት ከሚባለው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ቶን ፖታሽ ውስጥ 42 በመቶ ያህሉን በማልማት በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
2 መቶ አመታትን ሊያገለግል እንደሚችል የሚታሰበው ይህ ተፈጥሯዊ ሃብት በፈረንጆቹ 2025 ከኤርትራ ጥቅል ሃገራዊ ምርት የ10 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑም ተነግሯል፡፡
የAFC ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን በግል የትዊተር ገጻቸው ያስቀመጡት የኤርትራው የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ተሳትፎው ዓለም አቀፍ ደረጃ አለው ያሉትን ግዙፍ ኢንቨስትመንት ተግባራዊነት በመደገፍ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
አዲስ የሰላምና የትብብር ንፋስ እየነፈሰበት በሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለምትገኘው ኤርትራ ኢንቨስትመንት እድገት የላቀ አበርክቶ አለውም ብለዋል፡፡
የፕሮጄክቱ ባለቤት የሆነው ኮሉሊ ማዕድን አክሲዮን ማህበር (Colluli Mining Share Company) በኤርትራ ብሄራዊ የማዕድን ኮርፖሬሽንና በSouth Boulder Mines-STB Eritrea Pty Ltd የ50-50 የአክሲዮን ድርሻ የተያዘ ነው፡፡