ኢትዮጵያ በመጪው የካቲት ወር የአፍሪካ ሀገራት የምድር ጦር ጉባኤን ታስተናግዳለች
በኢትዮጵያ የሚካሄደው የአፍሪካ ሀገራት የምድር ጦር ጉባኤ ጉባዔ በኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ እና በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ትብብር በአዲስ አበባ የሚካሄድ ነው፡፡
የጉባዔውን ዝግጅት በማስመልከትም በኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ የምድር ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሞላ ኃይለማርም እና በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ላፍቴ ፍሎራ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊደግፍ ስለሚችልበት ሁኔታም ምክክር ተደርጓል፡፡
ጉባዔው ለወታደራዊ አመራር ክህሎቶች ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ ይካሄዳል ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ላፍቴ ጠንካራ የወደፊት ወታደራዊ አመራሮችን በመፍጠር ረገድ የላቀ አበርክቶ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ላፍቴ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ያላትን ትብብርና ቁርጠኝነት ጠንቅቄ አውቃለሁም ብለዋል፡፡
ድንበር ዘለል ስለሆኑ የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች በሚመከርበት በዚህ ጉባዔ ከአህጉሪቱ የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የምድር ጦር አዛዦች ይሳተፉበታል፡፡
ጉባኤው ለ8ኛ ጊዜ የሚካሄድም ሲሆን ለ4 ቀናት እንደሚቆይ ከ'በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር' ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡