ህንድ ስደተኞችን በተመለከተ ከሰሞኑ ያደረገችው የህግ ማሻሻያ ህዝባዊ ቁጣን ቀሰቀሰ
ስደተኞችን የሚመለከት ነው የተባለለትን የህንድ የዜግነት ህግ በመቃወም ወደ አደባባዮች የወጡ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች ከፖሊስ ተጋጭተዋል፡፡
አዲሱ ህግ በዋናነት ሙስሊም ከሆኑ 3 ሀገራት ኃይማኖታዊ ስደት ገጥሟቸው ወደ ህንድ የገቡ ሙስሊም ያልሆኑ ስደተኞችን የሚመለከት ሲሆን ስደተኞቹ ዜግነት እንዲሰጣቸው የሚደነግግ ነው፡፡
ይህ ግን ህዝባዊ ቁጣን ቀስቅሶ ብዙዎች ወደ አደባባዮች ወጥተዋል፡፡ ቁጣው ወደ ሰሜናዊና ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ወደ ሀገሪቱ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች ጭምር ተንሰራፍቷል፡፡
በህንድ ዋና ከተማ ዴልሂ አውቶቡሶች ተቃጥለዋል መንገዶችም ተዘግተዋል፡፡ ፖሊስም ተቃዋሚዎቹን በጭስ ቦምብ ለመበተንና ለማሰር ጥረት እያደረገ ነው፡፡ የኢንተርኔት እና መሰል አገልግሎቶችም በበርካታ ከተሞች ተቋርጠዋል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም፣አሜሪካ እና ካናዳ ለዜጎቻቸው የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
5 ቀናትን በዘለቀው ተቃውሞ 6 ሰዎች መሞታቸውን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡
ዴልሂ ምን ገጠማት?
የታዋቂው እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ጃሚያ ሚሊያ ተማሪዎች ተቃውሞ ዛሬም ዳግም አገርሽቶ ተስተውሏል፡፡ ተማሪዎቹ ትናንት እሁድ ያደረጉት ሰልፍ ከፖሊስ ጋር በመጋጨት ቢጠናቀቅም ዛሬም ሰልፍ ወጥተዋል፡፡
ግጭቱን ማን እንደጀመረው በገልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም ፖሊስ ድንጋይ በሚወረዉሩበት ተማሪዎች ላይ አስለቃሽ ጢስን ይጠቀም እንደነበረ ነው የተነገረው፡፡አውቶብሶችና ሞተር ሳይክሎች መቃጠላቸውን የዘገቡ የአካባቢው ሚዲያዎች 60 ገደማ ሰዎች መጎዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በደቡባዊ ዴልሂ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ዛሬ ተዘግተው ውለዋል፡፡
የጃሚያ ሚሊያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞን በመደገፍም በታዋቂው የጃዋሃርላል ኔህሩ ዩኒቨርስቲ ጭምር የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
ደቡባዊቷን የሃገሩቱ ከተማ ሃይደራባድን ጨምሮ ተቃውሞው ሌሎች ከተሞችንም አዳርሷል፡፡
ህጋዊ ማሻሻያው ለምን ተቃውሞ ሊገጥመው ቻለ?
ህጉ በህገወጥ መንገድ ከባንግላዴሽ፣ፓኪስታንና አፍጋኒስታን ወደ ህንድ ለገቡ ሙስሊም ያልሆኑ ስደተኞች ዜግነትን የሚፈቅድ ነው፡፡
ይህ ከሂንዱይዝም ጋር የጠበቀ ቁርኝት ላለውና ለቀኝ ዘመሙ የሃገሪቱ መሪ ፓርቲ ባሃራቲያ ጃናታ (BJP) በኃይማኖታቸው ምክንያት ለሚሳደዱ ከለላን የሚሰጥ ነው፡፡
ማሻሻያውን ለሚተቹ ግን ይህ የሚዋጥ አይደለም፡፡ መንግስት ከያዛቸው እስልምናን የመግፋት አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው ህገመንግስታዊ መርሆዎችን ይጥሳል ሲሉም ይተቻሉ፡፡
ህጉ በተፈጥሮው የአግላይነት አዝማማሚያ እንደሚታይበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ከሰሞኑ አስታውቆ ነበር፡፡ የህንድ መንግስት ግን ይህን ይቃወማል፡፡ አናሳ አይደሉም የሚላቸው ሙስሊሞች በህጉ ሊሸፈኑ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሌለና ራሳቸውን መጠበቅ የሚችሉበት እድል ሰፊ እንደሆነም በምክኒያትነት ይጠቅሳል፡፡
ተቃዋሚዎቹ በበኩላቸው ከባንግላዴሽ በሚመጡ ሙስሊም ያልሆኑ ስደተኞች ሊዋጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
የመሬት ይዞታቸውንና ስራቸውን ከመጋፋትም በላይ ባህልና ማንነታቸውን ሊያጠፉ እንደሚችሉም ነው የሚከራከሩት፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ