በዩክሬን ኦደሳ ግዛት በደረሰ የሚሳየል ጥቃት 19 ሰዎች ሞቱ
ሚሳየሎቹ ከጥቁር ባህር የኦዴሳ ወደብ በስተደቡብ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን አፓርትመንት መምታታቸው ተገልጿል
ጥቃቱ ተፈጸመው ለዩክሬን 800 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያጸደቀው የማድሪዱ የኔቶ ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ መሆኑ ነው
በዩክሬን ኦደሳ ግዛት በደረሰ የሚሳዔል ጥቃት 19 ሰዎች ሲሞቱ በደርዘን የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ሮይተር ዘግቧል።
ይህ ዜና የወጣው የኔቶ መሪዎች በማድሪድ ሲያደርጉት የነበረውን ስብሰባ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን የኔቶ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ የሚውል የ800 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
ጆ-ባይደን "ከዩክሬን ጋር ያለንን ትስስር ይበልጥ እናጎለብታለን ፤ ይህም ዩክሬናውያን በሩሲያ እንዳመይሸነፉ እስክናረጋግጥ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል" ነበር ያሉት፡፡
ይህን ተከትሎም ታዲያ የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ የሚሳየል ጥቃት በዩክሬኗ ኦደሳ ግዛት ላይ እንደተፈጸመ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል /ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘግቧል፡፡
ሚሳዔሎቹ የተተኮሱት በዛሬው እለት ሲሆን፤ ከጥቁር ባህር የኦዴሳ ወደብ በስተደቡብ 80 ኪሎ ሜትር (50 ማይል) ርቀት ላይ የሚገኘውን አፓርትመንት ህንጻ እና የመዝናኛ ማእከልን መምታታቸው ተገልጸዋል፡፡
ጥቃቱ በዩክሬን ምድር በመካሄድ ላይ ያለውን ጦርነት ይበልጥ እንዳባበሰውም እየተነገረ ነው፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን ኪሪሎ ቲሞሼንኮ በቴሌግራም እንዳሰፈሩት አሁን ላይ የሟቾች ቁጥር ሁለት ልጆችን ጨምሮ 19 ደርሷል።
የኦዴሳ ወታደራዊ አስተዳደር ቃል አቀባይ ሰርጊ ብራቹክ በቴሌቭዥን ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት በቢልሆሮድ-ዲኒስትሮቭስኪ የተካሄደው ጥቃት ከጥቁር ባህር በበረሩ አውሮፕላኖች ነው ብለዋል።
የተተኮሱት ሚሳዔሎች "በጣም ከባድ እና ኃይለኛ" መሆናቸውም አክለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና አዛዥ ጄንስ ስቶልተንበርግ ከቀናት በፊት ዩክሬን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ 'ጭካኔ' እያጋጠማት ነው ማላተቸው ይታወሳል፡፡
ዋና አዛዡ ዩክሬን ከሩሲያ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየተሰነዘረባት በመሆኑ፤ የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬንን መደገፋቸው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የኔቶ አጋሮች የክሬምሊንን ሃይል ለማስቆም በሚደረገው ጥረት - ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን ከባድ እና ረጅም ርቀት የሚምዘገዘጉ መሳሪያዎችን ጨምሮ በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመቱ የጦር መሳሪያዎች ወደ ኪቭ ማስገባታቸው የሚታወቅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየተቀዳጀችው ያለው ወታደራዊ ድል ያሰጋው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጦሩን ቁጥር ከ40 ሺህ ወደ 300 ሺህ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡