ከ30 በላይ ሀገራትን ያቀፈው ኔቶ ላለፉት ሶስት ቀናት በስፔን ማድሪድ ለሶስት ቀናት መክሯል
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ በስፔኗ መዲና ማድሪድ ላለፉት ሶስት ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ አጠናቋል፡፡
ከ30 በላይ ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው ኔቶ ላለፉት ሶስት ቀናት ባካሄደው ጉባኤ ላይ የሩሲያን እና ቻይናን ተጽዕኖ መግታት ላይ ያለሙ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ የሀገራት መሪዎች፣ የሀገራት ጦር መሪዎች፣ የወታደራዊ ሳይንስ ምሁራን እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈውበታል፡፡
መድረኩ ምዕራባዊያን ሀገራት የበለጠ የተደራጁበት እና አንድነታቸውን ያሳዩበት ጉባኤ መሆኑን ከጉባኤው በኋላ በወጡ ውሳኔዎች መረዳት ይቻላል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የዘንድሮው የኔቶ ጉባኤ ታሪካዊ እንደነበር ተናግረው ኔቶ አሁን ላይ ያለው የኔቶ አቋም ከ12 ዓመት በፊት የተነደፈ መሆኑን አክለዋል፡፡
የሩሲያ ዩክሬንን መውረር ኔቶን የበለጠ እንዳጠነከረው የተናገሩት ፕሬዝዳንት ባይደን ሩሲያ ምንግዜም የአውሮፓዊያን ጠላት መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲን በበኩላቸው ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን ቢቀላቀሉ የዩክሬንን ያህል ችግር አይፈጥርብንም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ይሁንና ኔቶ በስዊድን እና ፊንላንድ የጦር መሳሪያ ማዕከላትን እና ሌሎች ተያያዥ መሰረተ ልማቶችን የሚገነባ ከሆነ ሩሲያ ተመሳሳይ ምላሽ እንደምትስጥ ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለዋል፡፡
ኔቶ በማድሪዱ ጉባኤው ከወሰናቸው አዲስ ውሳኔዎች መካከል የጦር ሰራዊት አባላቱን ወደ 300 ሺህ እና በላይ እንዲሆን፣ ምዕራባዊያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከፍተኛ የደህንነት ችግር ውስጥ መግባታቸውን እና ለዚህም ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ከውሳኔዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የኔቶ ቋሚ መቀመጫ አሜሪካ እንዲቋቋም፣ በፖላንድ እና ብሪቴይን ውስጥ ላሉ የኔቶ ጦር ማዘዣዎች ተጨማሪ ጦር እና ሌሎች ድጋፎች እንዲደረጉም ተወስኗል፡፡
የኔቶ ኣባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡት ስዊድን እና ፊንላንድ ጥያቄን በመቀበል ማጽደቁም በማድሪዱ ጉባኤ ላይ ከተወሰኑ ጉዳዮች መካከል ዋኘኛው ነው፡፡
የሩሲያ እና ቻይና ግንኙነት የበለጠ እየጎለበተ መሄዱ ለምዕራባዊያን ሀገራት ትልቅ ስጋት መሆኑም በዚሁ ጉባኤ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በተለይም ከአውሮፓ ገበያ እየተወገደ ያለውን የሩሲያን ነዳጅ በከፍተኛ መጠን በቻይና ኩባንያዎች እየተገዛ መሆኑ ለምዕራባዊያን ትልቅ ስጋት እንደሆነ በማድሪዱ ጉባኤ ላይ አቋም ተይዟል፡፡
በተጨማሪም ኔቶ ከሩሲያ ጋ እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ስለሚደረግበት ሁኔታም የተወያዩ ሲሆን አውሮፓ ህብረት፣አሜሪካ፣እንግሊዝ እና ሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋልል፡፡