የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አራት ወር አልፎታል
አሜሪካ አምስት የቻይና ኩባንያዎች የሩሲያን ጦር እየደገፉ ነው ስትል ከሰሰች፡፡
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አምስት የቻይና ኩባንያዎች በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ላይ ለሩሲያ ጦር ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስታውቋል።
እነዚህ አምስት የቻይና ኩባንያዎች ማዕቀብ የተጣለባቸው ሲሆን፤ ቻይና ደግሞ ማዕቀቡ የዓለም አቀፍ ህግን የተከተለ አይደለም ስትል ውድቅ አድርጋለች፡፡
መሰረታቸውን ቻይና ያደረጉት እነዚህ አምስት ኩባንያዎች ማዕቀብ የተጣለበትን የሩሲያ መንግስት በመደገፍ የሩሲያ ጦር ድል እንዲቀዳጅ እያገዙ ናቸው መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ ንግድ ክፍል እንዳሳወቀው ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ በፊት ባሉት ቀናት ውስጥ ጀምሮ እስካሁን ድረስ መሰረታቸውን ቻይና ያደረጉ ኩባንያዎች ለሩሲያ ጦር ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን እያጓጓዙ ነው ብሏል፡፡
አሜሪካ ከእነዚህ አምስት ድርጅቶች በተጨማሪም በሌሎች ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን የሩሲያ፣ የዓረብ ኢምሬት፣ የሉቲንያ፣ፓኪስታን፣ሲናጋፖር፣ እንግሊዝ፣ ኡዝቤኪስታን እና ቬትናም ኩባያዎች ማዕቀቡ ተጥሎባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ አሜሪካ ማዕቀብ ከጣለችባቸው 36 ኩባንያዎች መካከል 25ቱ መቀመጫቸውን ቻይና ያደረጉ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ናቸው፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጃን በአሜሪካ የቀረበባቸውን ክሶች ውድቅ አድርገው ቻይና እና ሩሲያ በመደበኛ የንግድ ልውውጥ ውስጥ በመሆናቸው ይህ መደበኛ የንግድ ስራ እንጂ አሜሪካ እንደምትለው ህገወጥ እንቅስቃሴ አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡