ቱርክ ፊንላንድና ስዊድን ኔቶን እንዳይቀላቀሉ ስታቀርበው የነበረውን ተቃውሞ አነሳች
ቱርክ ተቃውሞዋን ያነሳቸው የኔቶ መሪዎች በስፔን ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ነው
ስዊደን እና ፊንላንድ ኔቶን ሲቀላቀሉ ኔቶ በባልቲክ ባህር ላይ ወታደራዊ የበላይነት ይኖረዋል ተብሏል
የኔቶ አጋር የሆነችው ቱርክ ፊንላንድና ስዊድን በምእራቡ አለም ያለውን ወታደራዊ ህብረት እንዳይቀላቀሉ ስታቀርበው የነበረውን ተቃውሞ አንስታለች፤ይህም ሁለቱ ሀገራት ወደ ህብረቱ እንዲቀላቀሉ መንገድ ተከፍቶላቸዋል፡፡
ቱርክ አቋሟን የቀየረችው ሀገራቱ አንዳቸው የአንዳቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ከተስማሙ በኋላ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የኔቶ መሪዎች በስፔን ከተሰበሰቡ ከአራት ሰአታት በኋላ ወደዚህ ስምምነት መድረሳቸውን እና ከሩሲያ የሚቃጣን ጥቃት ለመመከት በአሜሪካ የሚመራው ህብረት እንደሚያስፈልጋቸው ተስማምተዋል፡፡
ከስምምነቱ በኋላ ሄልሲንኪ እና ስቶክሆልም በኒውክሌር የታጠቀውን ህብረት ለመቀላቀል
ማመልከቻቸውን መቀጠል ይችላሉ፡፡ ለረጅም ጊዜ ገለልተኛ ሆነው የቆዩት ፊንላንድና ስዊድን ኔቶን እንዲቀላቀሉ መመቻቸቱ፤ ኑክሊየር ለታጠቀው ህብረት አዲስ ለውጥ ነው ተብሏል፡፡
"የእኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋ፡፡ ይህም ቱርክ... የፊንላንድ እና ስዊድን የኔቶ አባል እንዲሆኑ ግብዣውን እንደምትደግፍ" የፊንላንድ ፕሬዝዳንት ኒኒስቶ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
የፊንላንድ እና የስዊድን ኔቶ አባል ለመሆን የሚወስዱት እርምጃዎች በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ኒኒስቶ ተናግረዋል።
የኔቶ ዋና ፀሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ እና የቱርክ ፕሬዝዳንት በተለያዩ መግለጫዎች ስምምነቱን አረጋግጠዋል፡፡የኔቶ ሀላፊ ይህን ያሉት የቱርክ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ፣የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ማግዳሌና አንደርሰን እና ኒኒስቶ ከተነጋገሩ በኋላ ነው፡፡
የሁለቱ ሀገራት ኔቶን መቀላቀል በተለይም በባልቲክ ባህር ላይ ኔቶ ወታደራዊ የበላይት እንዲኖረው ያስችላል ተብላል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያካሄደች ባለችው ጦርነት ምክንያት ከምእራባውያን ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች፤ ምእራባውያንም ሩሲያን ያዳክማል ያሉትን ማእቀብ ሁሉ ጥለዋል፡፡