አውቶማቲክ መሳሪያ የያዙ ታጣቂዎች ትናንሽ ምሽት በቤተክርስቲያን እና በጥንታዊቷ ደርቤንት ከተማ በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ በመግባት ጥቃት ከፍተዋል
በሩሲያ ዳጋስታን ግዛት ውስጥ ታጣቂዎች በቤተክርስቲያን እና ምኩራብ ወይም አይሁድ ማምለኪያ ቦታ በፈጸሙት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 19 መድረሱ ተገለጸ።
አውቶማቲክ መሳሪያ የያዙ ታጣቂዎች ትናንሽ ምሽት በቤተክርስቲያን እና በጥንታዊቷ ደርቤንት ከተማ በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ በመግባት ጥቃት ከፍተዋል። ታጣቂዎቹ ወደ ቤተክርስቲያኗ ውስጥ በመግባት ኒኮላይ ኮትለኒኮቭ የተባሉ የ66 አመት ቄስ ከገደሉ በኋላ የቤተክርስቲያኗን ጉልላት አቃጥለዋል ተብሏል።
ታጣቂዎቹ ከሞስኮ በስተሰሜን በ125 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የካስፒያን ባህሩዋ ማካቻክላ ከተማ ቤተክርስቲያኗን ከማጥቃታቸው በፊት በትራፊክ ፖሊስ ጣቢያ ላይም ጥቃት ከፍተዋል።
በማቻክላ ከተማ በሚገኘው ቤተክርስያን ዙሪያ በተከፈተው ተኩስ ነዋሪዎች ህይወታቸውን ለማዳን ሲሮጡ እና ጭስ ሲወታጣ ታይቷል።
ለዚህ ጥቃት እስካሁን ኃላፊነቱን የወደሰደ የለም። የሩሲያ መርማሪ ቡድን እንደገለጸው በዚህ ጥቃት 15 ፖሊሶች እና አራት ንጹሃን ተገድለዋል።
"ይህ ለዳጋስታን እና ለመላ ሀገሪቱ የሀዘን ቀን ነው" ሲሉ የዳጋስታን ግዛት አስተዳዳሪ ሰርጌ ሚልኮቭ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪ የውጭ ኃይሎች ጥቃቱን በማድረስ መሳተፋቸውን ቢገልጹም፣ ዝርዝር ነገር አልሰጡም። በግዛቷ የሶስት ቀናት የሀዘን ቀን ታውጇል።
ምዕራባውያንን በካውካስ ግዛት የመገንጠል ጥያቄ እንዲነሳ እየጣሩ እንደሆነ የሚገልጹት ፑቲን በዳጋስታኑ ጥቃት ጉዳይ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
አብዛኛው ነዋሪዎቿ ሙስሊም የሆኑባት የዳጋስሳን ግዛት፣ በርካታ ጎሳዎች እና ቋንቋዎች ያሉባት በካስፒያን ባህር እና በጥቁር ባህር መካከል የሚገኝ ተራራማ ግዛት ነች።
በክርስቲያኖች እና በአይሁዶች ማምለኪያ ቦታዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት፣ ሩሲያ 145 ሰዎች ከተገደሉበት የሞስኮው የክሮከስ የሙዚቃ ድግስ ጥቃት ወዲህ አዲስ የእስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃት ሊያጋጥማት ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ባለፈው ጥር ወር የጋዛው ጦርነት በተከፈተበት ወቅት የፍልስጤምን ሰንደቅ አላማ የያዙ ተቃዋሚዎች ከቴልአቪቭ የመጡ አይሁድ መንገደኞችን ለማጥቃት ወደ ማካቻክላ አየርማረፊያ ጥሰው መግባታቸው ይታወሳል።