የአውሮፓ ህብረት ከዩክሬን በሚገቡ የግብርና ምርቶች ላይ ገደብ እንደሚጥል ገለጸ
ህብረቱ ገደቡን የሚጥለው የዩክሬን ግብርና ምርቶች ርካሽ መሆናቸውን ተከትሎ ነው
ገደቡ ካልተጣለ የአውሮፓ ሀገራት የገበሬዎች አመጽ ዳግም ሊቀሰቀስ እንደሚችል ተሰግቷል
የአውሮፓ ህብረት ከዩክሬን በሚገቡ የግብርና ምርቶች ላይ ገደብ እንደሚጥል ገለጸ፡፡
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት የኪቭን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በሚል ነበር የግብርና ምርቶች እንዲገቡ የፈቀደው፡፡
ህብረቱ በየዓመቱ ዩክሬን የግብርና ምርቶቿን ወደ አውሮፓ ሀገራት እንድታስገባ ኮታ በማስቀመጥ እድሉን ሰጥቶ ቆይቷል፡፡
ዩክሬንም ይህን እድል በመጠቀም እንቁላል፣ በቆሎ፣ ስኳር እና ሌሎች የግብርና ምርቶቿን በስፋት ወደ አውሮፓ ሀገራት ገበያዎች ስታስገባ ቆይታለች፡፡
ይሁንና የዩክሬን ምርቶች ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ሲነጻጸሩ ርካሽ በመሆናቸው የአውሮፓ ገበሬዎች ውሳኔውን ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡
ይህ ስጋት የገባው የአውሮፓ ህብረት በዩክሬን የግብርና ምርቶች ላይ ገደብ ሊጥል መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል ብትሆን የምታገኝው ጥቅም ምንድን ነው?
በዩክሬን ላይ የሚጣለው ገደብ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለ ሲሆን ኪቭ እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ያወጣችው መግለጫ የለም፡፡
ፖላንድን ጨምሮ አምስት የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በተናጥል የዩክሬን ግብርና ምርቶች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ እገዳ መጣላቸው ይታወሳል፡፡
ሀገራቱ እገዳውን የጣሉት ርካሽ የዩክሬን ምርቶች የሀገር ውስጥ ገበሬዎችን ከገበያ እና ውድድር ያስወጣል በሚል ነው፡፡