እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ልታቆም እንደምትችል አስታወቀች
ሀገሪቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ከሄዝቦላ ጋር ለሚኖር ግጭት ጦሯን ለማጠናከር ነው
በሄዝቦላ እና እስራኤል መካከል ታባብሶ የቀጠለው ውጥረት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና አዲስ ጦርነት እናዳያዋልድ አሰግቷል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የሚደረገው መጠነ ሰፊ ጥቃት ሊቆም እንደሚችል ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሀገራቸው በሰሜኑ በኩል ሄዝቦላ ለደቀነው የደህንነት ስጋት ምላሽ ለመስጠት በጋዛ የሚገኝውን ጦሯን ልትቀንስ እንደምትችል አስታውቀዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመርያ ግዜ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ኔታንያሁ ቻናል 14 ከተባለ የእስራኤል ቴሌቪዥን ጣብያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የጥቃቱን መጠን እንቀንሳለን ማለት ጦርነቱ አብቅቷል ማለት አይደለም ብለዋል፡፡
በጋዛ ሀማስን ሙሉ ለሙሉ እስከምናስወግድ እና ተጋቾችን እስከምናስመልስ ውግያው ይቀጥላል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰሜን ድንበር ላለው ስጋት መዘጋጀት በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሃማስ ጋር ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከፊል ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው በጦርነቱ መቀጠል ላይ ግን አሁንም አቋማቸውን አለመቀያራቸውን ነው አስረግጠው የተናገሩት፡፡
እየሩሳሌም እና ቴል አቪቭን ጨምሮ በ8 የእስራኤል ከተሞች ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ እና ህዝባዊ ተቃውሞ እያስተናገዱ የሚገኙት ኔታንያሁ ይህኛው ውሳኔያቸውም ነቀፌታን አስከትሎባቸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚንስትሩን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ መግለጫ ያወጣው ሀማስ ኔታንያሁ ለንግግር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እንዲሁም አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነትም ሆነ የጸጥታው ምክር ቤት ያጸደቀውን የውሳኔ ሀሳብ እንደማይቀበሉ ግልጽ ምላሽ የሰጡበት እንደሆነ ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡
የታጋች ቤተሰቦች ማህበር በበኩሉ የኔታንያሁ አስተዳደር ታጋቾችን ከሀማስ እጅ ሳያስለቅቅ ከጋዛ ጦሩን የሚያስወጣ ከሆነ ትልቅ ሀገራዊ እና ወታደራዊ ውድቀት ማሳያ ነው ብሏል፡፡
የጥቅምት ሰባቱን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ስታሰማራ ታጋቾችን ማስመለስ ፣ ሀማስን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት እና ድጋሚ ከፍልስጤም ጥቃት እንደማይሰነዘር ማረጋገጥ የሚሉ አላማዎችን ይዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የታጋች ቤተሰቦች ማህበር ባወጣው መግለጫ ታድያ “የ8ወራቱ ጦርነት ውጤት ምን እንደሆነ አስተዳደሩ ሊገልጽ ይገባል ፤ ሀማስ አሁንም አልጠፋም ታጋቾችም ለ8 ወራት ውስጥ በስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፤ ስለዚህ ዘመቻው ያመጣውን ስኬት አስተዳደሩ እንዲመልስልን እንፈልጋለን” ነው ያለው፡፡
14 ሺህ የሀማስ ታጣቂዎችን መግደሉን ያስታወቀው የእስራኤል ጦር በበኩሉ ሀማስን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም ሲል መናገሩ ይታወሳል፡፡
የጦሩ ቃል አቀባይ ሀማስ በሰዎች አይምሮ ውስጥ ያለ “አይዲዎሎጂ” ነው ሀማስን ማጥፋት ማለት ሙሉ የጋዛ ነዋሪዎችን ማጥፋት እንደማለት ነው በሚል ተናግረዋል፡፡ አክለውም “ከፍልስጤም ሊኖር የሚችል የጥቃት ስጋትን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት አይቻለም፤ የጥቅምት ሰባቱ አይነት ጥቃት እንዳይከሰት ማድረግ የምንችለው የተጠናከረ ዝግጅት እና ጥበቃ በማድረግ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
በመከላከያ ጦሩ እና በኔንታሁ አስተዳደር መካከል ያለው ስንጥቃት እየሰፋ ባለበት ቃል አቀባዩ አደረጉት የተባለው ንግግር በአስተዳደሩ ዘንድ ቁጣን አስነስቷል፡፡ የኔታንያሁ መንግስት ለዚህ በሰጠው ምላሽም የሀማሳ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እስኪበታተን ድረስ ውግያው ይቀጥላል ብሏል፡፡
ወደ ሰሜን ትኩረቴን አዞራለሁ ያለው የኔታንያሁ አስተዳደር በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው መመለስ እና የድንበር ጥበቃውን ማጠናከር አላማው እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡