በደቡብ ወሎ ደላንታ ኦፓል በማውጣት ላይ እያሉ መሬት ውስጥ የተቀበሩ 20 ወጣቶችን ህይወት ለማትረፍ ህዝቡ ሌት ተቀን እየቆፈረ ነው ተባለ
ወጣቶቹ ከአምስት ቀን በፊት ነበር ኦፓል ማዕድን ለማውጣት እየቆፈሩ እያሉ መሬቱ በዓለት የተደፈነባቸው
ከሶስት ዓመት በፊት ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሞ ከ11 ቀናት ቁፋሮ በኋላ ሁሉም በሕይወት ተገኝተው ነበር
በደቡብ ወሎ ደላንታ ኦፓል በማውጣት ላይ እያሉ መሬት ውስጥ የተቀበሩ 20 ወጣቶችን ህይወት ለማትረፍ ህዝቡ ሌት ተቀን እየቆፈረ ነው ተባለ፡፡
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ 018 ቀበሌ ልዩ ስሙ አለኋት ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ነበር ኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ ወጣቶች መውጫ ስፍራ በአለት የተደፈነባቸው፡፡
በማህበር ተደራጅተው ኦፓል እንዲያወጡ የተደራጁት እነዚህ ወጣቶች ቁጥራቸው 20 ሲሆን ከመሩት በህይወት ለማትረፍ የአካባቢው ማህበረሰብ ሌት ተቀን በፈረቃ እየቆፈረ መሆኑን የዞኑ መንግስት ኮሙንኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ እያሱ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ እያሱ ገለጻ ከሆነ ወጣቶቹ ሌሊት ላይ ማዕድኑን ለማውጣት እየቆፈሩ እያሉ መውጫቸው በዓለት የተዘጋ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ በተመሳሳይ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ጉዳዩን ለህዝብ አሳውቀዋል፡፡
ጥር 30 ቀን የተከሰተው ይህ አደጋ ከመሬት ውስጥ ባለው ዋሻ ውስጥ ያሉትን ወጣቶች የደላንታ ወረዳ እና የአካባቢው ማህበረሰብ በዘመቻ እየቆፈረ ነው የተባለ ሲሆን ወጣቶቹ ያሉት በግምት 750 ሜትር ርቀት ላይ ይሆናልም ተብሏል፡፡
እስካሁን በተደረገው ጥረትም 50 ሜትር ቁፋሮ እንደተቆፈረ የተናገሩት ሀላፊው ቦታው አለታማ እና የቁፋሮ ማሽን ለማስገባት አመቺ አለመሆኑ ጥሩን ፈታኝ አድርጎታል ሲሉም አክለዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ኦፓል ማዕድን በማውጣት ስራ ላይ የነበሩ ወጣቶች ተማሳሳይ አደጋ አጋጥሟቸው ነበር ያሉት አቶ እያሱ በተደረገው ርብርብ ከ11 ቀናት እልህ አስጨራሽ ቁፋሮ በኋላ ሁሉንም ወጣቶች በህይወት ማግኘት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
አቶ እያሱ አክለውም ወጣቶቹን በህይወት ለማትረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረው በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ሁሉንም ወጣቶች በህይወት ለመታደግ ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡