በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይራዘማል ብሎ እንደማይጠብቅ የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
ህብረቱ አዋጁ ጊዜው ሳይደርስ ሊነሳ እንደሚችል መንግስት ቃል ገብቶለት እንደነበርም አስታውቋል
በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ ሊጠናቀቅ ቀናት ቀርተውታል
በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይራዘማል ብሎ እንደማይጠብቅ የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡
ለስድስት ወራት ይቆያል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጠናቀቂያ ጊዜው የደረሰ ሲሆን ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም አዋጁ ስድስት ወራት ይሞለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በአዋጁ ዙሪያ እንዳለው አዋጁ ለተጨማሪ ጊዜ ይራዘማል ብሎ እንደማይጠብቅ አስታውቋል፡፡
በህብረቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሮላንድ ካቢያ ለአል ዐይን እንዳሉት “ኢትዮጵያ ከትግራይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ሌላ አስቸኳይ አዋጅ በመግባቷ እናዝናለን፣ በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት እንዲቆይ ተደርጎ ታወጀ እንጂ ጊዜው ከመድረሱ በፊት እንደሚነሳ በኢትዮጵያ መንግስት ተነግሮን ነበር“ ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሮላንድ አክለውም “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት እኛ እና አጋሮቻችን ስራችንን እንደልብ ተንቀሳቅሰን እንዳነሰራ አድርጓል፣ መንግስትም የአማራ ክልል ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን በመናገሩ ምክንያት አዋጁን ለተጨማሪ ጊዜ ያራዝማል የሚል ተስፋ የለኝም“ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በርካታ ኢትዮጵያዊን በጦርነት እና መፈናቀል እየተፈተኑ ነው ያሉት አምባሳደር ሮላንድ ካቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የዜጎች መብቶች ከመገደብ አልፎ ለእንግልት እንዲዳረጉ በር ይከፍታልም ብለዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ በበኩላቸው አስፈጻሚው እስካሁን በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ ወይም ይራዘም የሚለውን ጉዳይ እንዳላቀረበላቸው ነግረውናል፡፡
“የአስቸኳይ አዋጁ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ገና ስለሆነ ምን አልባት እየተገመገመ ሊሆን ይችላል” ያሉን ፕሮፌሰር ምህረቱ ጉዳዩን የማቅረብ ሀላፊነቱ የአስፈጻሚው አካል ነውም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የፌደራል መንግስት ከዚህ በፊት በሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን መናገራቸው ይታወሳል፡፡