በትግራይና አማራ ክልሎች 400 የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ
ተቋሙ በሁለቱ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ ያደረሰውን ጉዳት ይፋ አድርጓል
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በክልሎቹ የተከሰተው “ድርቅ ወይስ ረሃብ” ከሚለው የቃላት ምልልስ በመውጣት ለተጎጂዎች በፍጥነት መድረስ ይገባል ብሏል
በትግራይና አማራ ክልሎች 400 የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ።
ተቋሙ ድርቅ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎችን ልኮ ምልከታ ማድረጉን ባስታወቀበት መግለጫው፥ የአሰራር ክፍተቶች ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አመላክቷል።
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በትግራይና አማራ ክልሎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ያደረሰውን ጉዳትም በመግለጫው ጠቁሟል።
ተቋሙ በትግራይ ክልል በአበርገሌና ኢስራ ወአዲ ወጅራት ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 351 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ከ15 ሺህ በላይ ከወረዳዎቹ መፈናቀላቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት 5 ሺህ 518 ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውንም ገልጿል።
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በአማራ ክልልም ከተከሰተው ድርቅ ጋር በተያያዘ የ44 ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው በመግለጫው የጠቆመው።
በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 43 ወረዳዎች ከ325 ሺህ ሄክታር በላይ የሰብል ማሳ ሙሉ በሙሉ ከምርት ውጪ በመሆኑ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለችግር መጋለጣቸውን ነው ያብራራው።
የክልሉ መንግሥት በድርቅ ምክንያት የሞተ ሰው የለም የሚል መግለጫን ቢያወጣም ተቋሙ ናሙና ወሰድኩባቸው ባላቸው የሰሜን ጎንደር እና የዋግኽምራ ዞኖች 21 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን ማረጋገጡንም ጠቁሟል።
በዋግህምራ ዞን አበርገሌ ወረዳ 12 ሺህ 270 ፤ በሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ 9100 ሰዎች መፈናቀላቸውንና ይህም የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ከገለጸው መረጃ የሚቃረን መሆኑንም በማንሳት።
የክልሊ መንግስት የመጠለያ ጣቢያ አያስፈልግም የሚል አቅጣጫ መስጠቱም ተፈናቃዮች በተደራጀ መልኩ አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል ሲል ወቅሷል።
የተረጂዎች ቁጥር ልየታ፤ የ”ድርቅና ረሃብ” ብያኔ
በፌደራሉ መንግስትና የድርቅ አደጋ በተከሰተባቸው የትግራይና አማራ ክልሎች በተጎጂዎች ቁጥርም ሆነ በአደጋው ብያኔ ዙሪያ ልዩነቶች ይስተዋላሉ።
የፌዴራሉ መንግስት በትግራይ ክልል ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ናቸው ሲል፥ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ቁጥሩን 4 ነጥብ 2 ሚሊየን አድርሶታል።
በአማራ ክልልም የተጎጂዎች ልየታ ላይ በክልሉ አደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና እንዲሁም በዞን እና በወረዳዎች መካከል አለመናበብ መኖሩን የሚያነሳው የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም፥ በድርቅ ምክንያት የሞተ እና የተፈናቀለ ሰው የሚሉ መግለጫዎች ሲወጡ እንደነበር አስታውሷል።
የተረጂዎች ልየታ አሃዝ ላይ የሚታዩ ልዩነቶች በእርዳታ ስርጭትና አቅርቦት ላይ እክል መፍጠሩንም ተቋሙ በመግለጫው ጠቁሟል።
በክልሎቹ የተከሰተው “ድርቅ” ነው ወይስ “ረሃብ” የሚለው የብያኔ ልዩነትም ለተጎጂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ ለማቅረብ ባለማስቻሉ በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከ1977ቱ የከፋ ድርቅና ረሃብ ሊከሰት ጫፍ ላይ ደርሷል የሚል መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ የፌደራሉ መንግስት “ሀሰተኛ እና ችግሩን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ ነው” በሚል ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ግን “ድርቅ ወይስ ረሃብ ከሚለው የቃላት ምልልስ” በመውጣት ችግሩ የከፋ ጉዳት ሳያመጣ ለተጎጂዎች ፈጣን ድጋፍ እንዲደረግ አሳስቧል።
የፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚያደርጋቸው ድጋፎች ለተገቢው አካል መድረሱን የሚያረጋግጥበት የቁጥጥር ዘዴ ደካማ መሆን አለማቀፍ የረድኤት ድርጅቶች አመኔታ እንዳይኖራቸው ማድረጉን የጠቀሰው ተቋሙ፥ የቁጥጥር ስርአቱ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል ብሏል።
በኢትዮጵያ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።