የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ እንደሚያሳስበው ኢሰመኮ ገለጸ
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአራት ወራት አራዘመ
ዶ/ር ዳንኤል “የአዋጁ መራዘም በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ አሳሳቢ ነው” ብለዋል
የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ አሳሳቢ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ባሳለፍነው ነሀሴ ለስድስት ወራት የታወጀው አስቸኳይ አዋጅ ለተጨማሪ ወራት ተራዝሟል።
የምክር ቤቱ አባላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ አደረጉት በተባለው ውይይት ከዋጁ በሁለት ተቃውሞ በሶሰት ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ለአራት ወራት እንዲራዘም መወሰኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በኤክስ የቀድሞ ትዊተር ገጻው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ዳንኤል “የአዋጁ መራዘም በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “የግጭት ተጎጂ በሆኑ፣ በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ባሉ እና ለፍርድ ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜያት በእስር ላይ በሚቆዩ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተጽእኖ አሳሳቢ” ብለዋል።
ስለዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት እና ተመጣጣኝነትን ሊያጤኑ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ውይይት እና ንግር ለሁሉም ነገር ቁልፍ መሆኑንም ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ አስታውቀዋል።
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል።
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር።
ባለፉት ስድስት ወራት ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር በተያያዘ በባህር ዳር ፣ በጎንደር እና በኮምቦልቻ ከተሞች 706 ሰዎች መታሰራውን የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ጌዴዮን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።