5 ተጨማሪ ላቦራቶሪዎች በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሏል
በዚህ ሳምንት ተጨማሪ 12 ላቦራቶሪዎች ሥራ ጀምረዋል
የኮቪድ-19 ምርመራ አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ 12 ላቦራቶሪዎች በዚህ ሳምንት ሥራ መጀመራቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የላቦራቶሪዎች ቁጥር 20 የደረሰ ሲሆን፣ ተጨማሪ አምስት ላቦራቶሪዎች በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በቀጣይ ለላቦራቶሪዎቹ አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት ከተለያዩ አገራት ጋር ንግግር መጀመሩንም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
ዶ/ር ሊያ ከላቦራቶሪዎቹ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በጤና ጣቢያዎች ጭምር ከሳንባ በሽታና ሳል ጋር የተያያዙ ምልክቶችን ናሙና ወስዶ መመርመር መጀመሩንም አስረድተዋል።
ለቫይረሱ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የቤት ለቤት ምርመራዎችን በማካሄድ የበሽታውን ደረጃ ለማወቅ የሚከናወነው ተግባርም ተጠናክሮ ቀጥሏል እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ፡፡
አንድ ሺ ታማሚዎችን እንዲያስተናግድ ሆኖ በመዘጋጀት ላይ ያለውን ሚሊኒየም አዳራሽን ጨምሮ ሌሎች የኮቪድ-19 ለይቶ ማከሚያ ተቋማትን የማጠናከሩ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ-19 ምርመራ ማዕከል የሚጠበቀዉን ስታንዳርድና ግብዓት በማሟላት እንዲሁም የሰዉ ሃይል ስልጠናና ዝግጅት ተደርጎ አገልግሎት ስራ መጀመሩን ትናንት ማስታወቁም ይታወሳል፡፡