አዲስ የተለዩትን ዘጠኝ ተጠቂዎች ጨምሮ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 65 ደርሷል
አዲስ የተለዩትን ዘጠኝ ተጠቂዎች ጨምሮ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 65 ደርሷል
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 442 ሰዎች መካከል ዘጠኙ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 65 ከፍ ብሏል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፣ ዛሬ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠው ሁሉም ግለሰቦች የጉዞ ታሪክ አላቸው።
ከግለሰቦቹ መካከል ሰባቱ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ፣ አንድ ኤርትራዊ ቀሪዋ ደግሞ የህንድ ዜግነት ያላት ናት።
አራቱ ኢትዮጵያዊያን ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በለይቶ ማቆያ ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ሁለቱ የቱርክ፣ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ደግሞ የእንግሊዝ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን፣ ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን አውስተዋል።
የ20 ዓመቷ ህንዳዊት የአሜሪካ እንዲሁም የ40 ዓመቱ ኤርትራዊ ደግሞ የዱባይ ጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
በጽኑ ህሙማን ክፍል ከሚገኙት ሁለት ግለሰቦች መካከል አንዱ የጤና መሻሻል በማሳየቱ ከክፍሉ መውጣቱንም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም በኢትዮጵያ 3 ሺ 232 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 57ቱ የህክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
አራት ግለሰቦች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፣ ሁለቱ በበሽታው ህይወታቸው ሲያልፍ ሌላ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ አገራቸው መሸኘታቸው ይታወቃል።
የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን የጨረሱ 554 ግለሰቦች በትናንትናው እለት ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉም ይታወቃል፡፡