የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን የጨረሱ 554 ግለሰቦች ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ
የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን የጨረሱ 554 ግለሰቦች ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ
ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የኮሮናቫይረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዳይስፋፋ ከሚያደርጉ የዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሃሳቦች ውስጥ የለይቶ ማቆያ አንዱ ነው።
በሀገሪቱም የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ በኋላ በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁሉም ከውጭ የሚመጡት መንገደኞች በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ተወስኗል ብለዋል።
ይህም ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን በሠላም ሚኒስቴር አስተባበሪነት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከጸጥታ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጰያ የመጡ መንገደኞች በራሳቸው ወጪ በሆቴሎች ክትትል እየተደረገለቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአስገዳጅ ሁኔታ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን በዩኒቨርሲቲዎችና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመንግሥት ወጪ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የአስገዳጅ የለይቶ ማቆያው ከተጀመረ እስካሁን ድረስ አስፈላጊ ምርመራ ተድርጎላቸው 14 ቀን የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን የጨረሱ 554 ሰዎች ከለይቶ መቆያ መውጣታቸውን ጠቁመዋል።
የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን የጨረሱት ግለሰቦች ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ ኅብረተሰቡ ከመድሎና ማግለል ነጻ በሆነ አኳኋን ሊቀበላቸው ይገባል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በአሁኑ ወቅት 2 ሺህ 36 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስፈላጊው የጤና ክትትል በባለሙያዎች እየተደረገባቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የተጀመረው የ14 ቀናት የለይቶ ማቆያም የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረግ መቻሉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 56 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ከእነዚህም ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፣ ሁለቱ በጽኑ ህሙማን ክፍል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሆኗል፡፡ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 90 ሺ ገደማ ደርሷል፡፡