ባለፉት 24 ሰዓታት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሶስቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ናቸው
ባለፉት 24 ሰዓታት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሶስቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ናቸው
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 225 ሰዎች ውስጥ 3 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠ ሲሆን አጠቃላይ ቁጥሩም ወደ 55 ከፍ ብሏል።
ሶስቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ሁለቱ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
ሁለቱ ግለሰቦች የ29 ዓመት እድሜ ያላቸውና ከዱባይ መጥተው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ ናቸው፡፡
አንዱ ግለሰብ የ36 ዓመት እድሜ ያለውና በአማራ ክልል የአዊ ዞን አዲስ ቅዳምን ከተማ ነዋሪ ነው። ግለሰቡ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን፤ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳለው ተጠርጥሮ ምርመራ እንደተደረገለት ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፣ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ እስካሁን ባለው ሂደት ለ2 ሺህ 496 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል። አንድ ተጨማሪ ሰው ወደ ጽኑ ህሙማን ማቆያ የገባ ሲሆን በድምሩ 2 ሰዎች በጽኑ ህሙማን ማቆያው ይገኛሉ፡፡
ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል አንድ ሰው ወደ ጽኑ ህሙማን ማቆያ መግባቱንና ይህም በጽኑ ህሙማን መቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ቁጥር 2 እንዳደረሰው ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች ባሉበት ክልል በተዘጋጀ የነጻ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
ህብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግም ነው ያሳሰቡት።
በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል አራቱ ያገገሙ ሲሆን፣ ሁለቱ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ አገራቸው ተሸኝተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ዛሬ መጋቢት 30/2012 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ የሚያካትታቸው ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አልተደረጉም፡፡