27ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ ከተማ ተጀመረ
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከሻርም ኤል ሼክ ጉባኤ ብዙ እንደሚጠበቅ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል
በጉባኤው ከ190 ሀገራት የተውጣጡ ውሳኔ ሰጪዎችን እና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል
የዓለም ሀገራት በተለያዩ የአየር ንብረት አንኳር ጉዳዮች ላይ የሚመክሩበት 27ኛው የመድ የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ-27) በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
ከ190 ሀገራት የተውጣጡ የውሳኔ ሰጪዎችን እና ባለሙያዎችን የሚያሳትፈው ጉባኤው እስከ ህዳር 18 የሚቆይ ሲሆን በአሳሳቢው አየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ተሳታፊዎቹ በፓሪስ ስምምነት ግቦች ላይ መሰረት በማድረግ የዓለም ሙቀት መጨመር በ 1ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺዬስ ለመገደብ በሚቻልበት ሁኔታ እንዲሁም ቃል በተገባው መሰረት የበለጸጉ ሀገራት የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ ተፈጻሚ በሚያደርጉበት አጀንዳ ላይ እንደሚመክሩም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የበለጸጉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የገቡትን ቃል ለመተግበር በመዘግየታቸው ዓለማችን ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባታል ሲሉ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በፓሪሱ ጉባኤ የበለጸጉ ሀገራት እያደጉ ላሉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም በቃላቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ በተለያየ መልኩ ሲገለጽ ቆይቷል።
በዚህ ስጋት የገባቸው ተመድ መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን በማስመለከት በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤ ዓለም ወደ ተግባር ካልገባ የሚመጣው አደጋ ከዚህም የባሰ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የፓኪስታን አንድ ሶስተኛ ክፍል በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በአውሮፓ በ500 ዓመታት ውስጥ ያጋጠመው የበጋ ወቅት እንዲሁም መላው ኩባ እና አሜሪካ ኢያን እየደረሰ ያከው የአውሎ ነፋስ አደጋ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች ናቸው ያሉት ዋና ጸኃፊው፤ ችግሩን ለመቅረፍ የሚወሰዱ እርመጃዎች በቂ አይደሉም ሲሉም ነበር የተናገሩት ጉቴሬዝ፡፡
“የአየር ንብረት ትርምስ ወደፊት እየገሰገሰ ቢሆንም የሚወሰደው ርምጃ ቆሟል” ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ በዛሬው እለት የጀመረው የግብጽ ሻርም ኤል-ሼክ የአየር ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-27) ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ስሚወሰደው እርምጃ ቅድሚያ ሰጥተው የሚመክሩበት ወሳኝ ጉባኤ መሆን እንዳለበትም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ዋና ጸሃፊው፤ "የልቀት መጠኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ ነው፤ ጣት ሳንቀሳሰር መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅብናል” ሲሉም አሳስበዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፤ ዓለማችን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺዬስ ገዳማ ጨምራለች። ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠንም በ50 በመቶ ጨምሯል።