በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ሶስት የቢሆን ግምቶች
በኢራን እና እስራኤል ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎች ቴል አቪቭ እና ቴህራን ሊወስዱት የሚችሉትን ቀጣይ እርምጃ ለአል ዐይን ኒውስ አጋርተዋል
18ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ከ5 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል
ጋዛ በአምስት አስርት አመታት ታይቶ በማይታወቅ ጦርነት እየታመሰች ነው።
ሃማስ ከ18 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ የወሰደውን ያልተጠበቀ ጥቃት ተከትሎ ቴል አቪቭ የማያቋርጥ የአየር ድብደባ እየፈጸመች ትገኛለች።
አሜሪካን ጨምሮ የብሪታንያ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ መሪዎችም ቴል አቪቭ ድረስ በመገኘት ከእስራኤል ጎን እንደሚሰለፉ ቃል ገብተዋል።
ኳታር፣ ኢራን እና ቱርክን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትም በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ ላይ ናቸው።
ጦርነቱ ቀጠናውን እንዳያተራምስም ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢራን ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚሰጡት ዶክተር አሪፍ ናስርም በዚህ ጦርነት ሶስት ጉዳዮች ይጠበቃሉ ብለዋል።
የመጀመሪያው ሄዝቦላህ ጦርነቱን የመቀላቀሉ ጉዳይ ነው፤ እስራኤል በጋዛ የምድር ውጊያ እንደጀመረች ጦርነቱን በይፋ እቀላቀላለሁ ያለው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጦርነቱን ከተቀላቀለ የተዋናዮቹ ቁጥር መጨመሩ አይቀርም ይላሉ ዶክተር ናስር።
የተንታኙ ሁለተኛው የቢሆን ግምት እስራኤል በኢራን የተለያዩ ወታደራዊ መሰረተልማቶች ላይ ጥቃት ልታደርስ ትችላለች የሚለው ነው። ቴህራን የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ታጣቂዎችን እንደምትደግፍ ይነገራል። በሊባኖሱ የሚገኙ በቴህራን ድጋፍ የተቋቋሙ መሰረተ ልማቶችን መምታት ሄዝቦላህን ያዳክመዋል በሚል ቴል አቪቭ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች።
ሶስተኛው ግምታቸው ደግሞ በሃማስ የታገቱትን ሰዎች ለማስለቀቅ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ትደርሳለች የሚል ነው፤ ይሁን እንጂ ይሄኛው የመሳካት እድሉ ዝቅተኛ ነው ይላሉ ዶክተር አሪፍ ናስር።
በአል አህራም የፖለቲካ እና ስትራቴጂ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል የእስራኤል ጉዳዮች አጥኝው ዶክተር ሳይድ ኦካሻ በበኩላቸው ኢራን ሶስት ከባድ አማራጮች እንዳሏት ያነሳሉ።
የመጀመሪያው ለሃማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ በእስራኤል እንዲዳከሙ እና ሃማስ በጋዛ ሰርጥ ያለውን መሪነት እስኪያበቃ በዝምታ ማየት ነው። ይህም በፍልስጤም ምድር ምንም አይነት ተገዳዳሪ ሃይል እንዳይኖራት ያደርጋል።
ሁለተኛው ደግሞ የሊባኖሱን ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል ጦርነት እንዲከፍት ማድረግ ነው።
ሶስተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ግን እስራኤል ላይ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃት በመፈጸም ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ምድር ዘልቆ ገብቶ እንዲዋጋ ማድረግ ነው ይላሉ ዶክተር ሳይድ።
የአሜሪካ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ተሳትፎ መቀጠልም ቴህራን ሁለተኛውን አልያም ሶስተኛውን አማራጭ እንድትጠቀም ሊያደርጋት ይችላል ብለዋል።