ማክሮን አይኤስን ለመዋጋት የተቋቋመው ጥምረት ሀማስንም ሊያጠቃልል እንደሚገባ ገለጹ
ማክሮን ይህን ያሉት ሀማስን እየተዋጋች ያለችውን እስራኤል በጎበኙበት ወቅት ነው
ከማክሮን ቀደም ብሎ የአሜሪካ፣ የጀርመን እና የእንግሊዝ መሪዎች እስራኤልን ጎብኝተዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን አይኤስን የሚዋጋው አለምአቀፍ ጥምረት ሀማስንም መዋጋት አለበት የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
ማክሮን ይህን ያሉት ሀማስን እየተዋጋች ያለችውን እስራኤል በጎበኙበት ወቅት ነው።
ማክሮን ወደ እስራኤል ያቀኑት ከሀማስ ጋር ጦርነት እያደረገች ላለችው ቴል አቪቭ ድጋፍ ለመስጠትና እና አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ማክሮን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በመሆን በሰጡት የጋራ መግለጫ "ይህ ዘግናኝ የሆነ የሽብርተኝነት ጥቃት ነው፤ ሰዎችን ማገት ምን ማለት እንደሆነ እናውቃለን። ዘጠኝ ፈረንሳያውያን ታግተዋል፤ እናም ይህን ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለንም። ነጻ ለማድረግ ሀሉንም ነገር እናደርጋለን" ብለዋል።
አይኤስን ለመዋጋት አለምአቀፍ ጥምረት እንዳለ የገለጹት ማክሮን ሀማስንም መዋጋት አለብን ብለዋል።
ማክሮን አለምአቀፍ ጥምረት የሚሉት ፈረንሳይን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ ሀገራት ያሉበት እና በአሜሪካ የሚመራውን ጥምረት ነው።
ፕሬዝደንት ማክሮን የሊባኖሱ ሂዝቦላ፣ ኢራን እና የየመኑ ሆውዚ ታጣቂ በግዴለሽነት አዲስ የውጊያ ግንባር እንዳይከፍቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁም ሄዝቦላ ይህን ጦርነት የሚቀላቀል ከሆነ እንደሚጸጸት አሳስበዋል።
ኔታንያሁ አክለውም "ሄዝቦላ የሚቀላቀል ከሆነ ውድመቱ ከባድ ይሆናል። ያዳምጡናል ብየ አስባለሁ"።
የፈረንሳዩ ጋዜጣ ሊሞንዴ እንደዘገበው ማክሮን በእስራኤል ቆይታቸው በሀማስ ጥቃት ሰለባ ከሆኑ ፈረንሳያውያን ቤተሰቦች ጋር ተገናኝተዋል።
ከማክሮን ቀደም ብሎ የአሜሪካ፣ የጀርመን እና የእንግሊዝ መሪዎች እስራኤልን ጎብኝተዋል።