የጥይት ድምጾች የማይሰሙባት አፍሪካን እውን ማድረግ ይቻላልን?
ግጭትና አፍሪካ
የዛሬ ሰባት ዓመት እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጀት፣ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበት 50ኛ ዓመት ሲከበር የአፍሪካ መሪዎች በወቅቱ አንድ ቃል ገቡ፤ ይሄም በ2020 (ዘንድሮ ማለት ነው) የጥይት ድምጽ የማይሰማባትን አፍሪካ እውን እናደርጋለን የሚል ነው፡፡
መሪዎቹ ከዚህ ስምምነት ላይ በደረሱበት በዚያን ጊዜ በአህጉሪቱ በጦር መሳሪያ የታገዙ በጣት የሚቆጠሩ ጦርነቶች ነበሩ፡፡
ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አሳይቶ እንደማያውቅ በብዙዎች የሚተቸውና "ጥርስ የሌለው አንበሳ" በመባልም የሚታወቀው የአፍሪካ ህብረት አህጉሪቱን የተኩስ ድምጽ የማይሰማባት እና ከግጭት የጸዳች አደርጋታለሁ ባለበት በዘንድሮ ዓመት የጥይት ድምጾች ይበልት ተበራክተዋል፡፡
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የዓለም ሰላም ጥናት ተቋም መረጃ እንደሚያመለክተው እንደ አውሮፓውያኑ በ2005 በአህጉረ አፍሪካ በ 6 ሀገራት 7 ግጭቶች የነበሩ ሲሆን ዘንድሮ በ2020 ደግሞ በ300% ወይም በ3 እጥፍ አድጎ በ17 ሀገራት 21 በጦር መሳሪያ የታጀቡ ጦርነቶችን አህጉሪቱ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡
አህጉሪቱ ከዓመታዊ በጀቷ 15 በመቶ የሚሆነውን ለጦር መሳሪያ ግዢ እንደምታውልም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡
በሌላ በኩል በዚህች ተአምራዊ አህጉር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በልቶ ለማደር የምግብ እርዳታ ይጠብቃል፡፡ ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን በምግብ ዋስትናና ስርዓተ ምግብ ላይ በተደረገ ውይይት፣ ከሰሀራ በታች አፍሪካ 239 ሚሊየን ህዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገልጿል፡፡
ለአህጉሪቱ የከፋ የምግብ እጥረት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥና የኢኮኖሚ ችግር በተጨማሪ ምክኒያትነት ቢጠቀሱም፣ ግጭት ዋነኛው ምክኒያት ነው፡፡
33ኛው የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳዎች
የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካ
በየዓመቱ በተከሸኑ ቃላት የታጀበ መሪ ቃል ይዞ በመቅረብ የማይታማው የአፍሪካ ህብረት የዘንድሮውን 33ኛውን የመሪዎች ጉባኤም፣ የጥይት ድምጽ የማይሰማባት፡ ለልማት ምቹ የሆነች አፍሪካን መፍጠር በሚል መሪ ቃል ነው በማካሄድ ላይ የሚገኘው፡፡ የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳም ይሄው ሀሳብ ነው፡፡
በርግጥም ግጭት፣ ጦርነት፣ የጥይት ድምጽ መገለጫዋ ለሆነ አህጉር መሪ ቃሉ እጅግ የሚያማልል ነው፡፡ ጥያቄው ከቃል ያለፈ ተግባር መቼና በማን እውን ሊሆን ይችላል የሚለው ነው፡፡
የጉባኤውን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት አፍሪካን ከተኩስ ለማላቀቅም ሆነ በየቀጣናው ከሚታዩ ሌሎች ችግሮቿ ለማላቀቅ ወንድማማችነትን ማጎልበት የግድ ይላል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔን ማምጣት እና የሌሎችን ጣልቃ ገብነት ማስቆም ከአህጉሪቱ ሀገራት የሚጠበቅ እንደሆነም ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ የህብረቱ የ2019 ሊቀመንበር የነበሩት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታ አል ሲሲ፣ የህብረቱ የ2020 አዲስ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ እና ሌሎችም ንግግር የማድረግ እድል ያገኙ ባለስልጣናት በዚህ ሀሳብ ይስማመሉ፡፡
በአህጉሪቱ ጉዳይ ጣልቃ የማይገባበትን ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር ምን ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ግን ማንም ሀሳብ አልሰጠም፡፡
የተለያዩ ሀገራት ገብተው የሚፈተፍቱበት ወቅታዊው የሊቢያ ጉዳይ ለውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ሁነኛ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ምናልባት የመሪዎቹ ቀጣይ ውይይት በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳች ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚችል ይጠበቃል፤ ምንም እንኳን እስካሁን በአህጉሪቱ ጉዳይ በሌሎች ሀገራት ለሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች ህብረቱ ተግባራዊ ምላሽ የሰጠበት ጊዜ ባይታወቅም፡፡
የህብረቱ አባል ሀገራት ለገቡት ቃል ተገዢ አለመሆናቸው ሌላው ለአህጉሪቱ ሰላም መራቅ ከሚጠቀሱት መመካከል ነው። አዲሱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎዛ በሊቢያ፣ በደቡብ ሱዳንና ሌሎችም ግጭት ያለባቸው ሀገራት እልባት ለማምጣት ከሚሰሩ አጋር አካላት ጋር በትብብር በመስራት የጥይት ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን በፍጥነት እውን ለማድረግ ዛሬውኑ ስራችንን በቁርጠኝነት መጀመር አለብን ያሉትም ለዚህ ነው።
ሌሎች የጉባኤው ጉዳዮች
አዲሱ የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ ሁሉም በአንድ ድምጽ ያወገዙት፣ ከአፍሪካ ጉዳዮች ባልተናነሰ መልኩ ትኩረት ሰጥተውበት ንግግር ያደረጉበት ነጥብ ነው፡፡ አዲሱ የህብረቱ ሊቀመንበር ሲርል ራማፎዛ የአሜሪካን ውሳኔ ሀገራቸው ካሳለፈችው የአፓርታይድ ወቅት ጋር አነጻጽረው ኮንነዋል፡፡
ሁሉንም አካላት ያላሳተፈ እቅድ ፈጽሞ ተቀባይነት የማይኖረው ነው ያሉት ራማፎዛ እቅዱ እስራኤልን ብቻ የሚጠቅም የፍልስጥኤምን ነጻነት ፈጽሞ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲሉ ኮንነውታል፡፡
በመድረኩ እድል የተሰጣቸው የፍልስጥኤም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር መሀመድ እሽቴ ሰው በዳቦ ብቻ እንደማይኖር ከኢየሱስ ክርስቶስ፣ አብሮ ስለመኖር ደግሞ ከነቢዩ መሀመድ ተምረናል፤ በመሆኑም ነጻነት አግኝተን ከሁሉም ጋር በትብብር መኖር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
አፍሪካ ከጎናቸው በመሆኑም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የሴቶች ጉዳይ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የህብረቱ ማሻሻያ ሌሎች በጉባኤው ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይም ህብረቱ የጋራ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡
"ጥርስ የሌለው አንበሳ" ጥርስ አውጥቶ እናየው ይሆን? ተስፋ ሰጭ ምላሽ ማግኘት ይቸግራል፡፡