የ340 ሚሊየን ዶላር ሎተሪ አሸናፊ መሆንዎ ድረገጽ ላይ ተለጥፎ “በስህተት ነው” ቢባሉ ምን ያደርጋሉ?
የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪው ባንክ እከፍትበታለሁ ያለውን ገንዘብ ለመውሰድ ወደ ሎተሪ ድርጅቱ ሲያመራ ያልጠበቀውን ምላሽ አግኝቷል
ግለሰቡ “ህልሜን አጨልሟል” ባለው የሎተሪ ድርጅት ላይ ክስ መስርቷል
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆነው ጆን ቺክስ ባለፈው አመት በቆረጠው ሎተሪ የ340 ሚሊየን ዶላር ጃክፖት አሸናፊ መሆኑን ሲመለከት ሰውነቱ መራዱን ያስታውሳል።
ድረ ገጽ ላይ የወጡት የፖወርቦል ሎተሪ አሸናፊ ቁጥሮቹ ከቆረጠው ትኬት ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ደጋግሞ ከተመለከተ በኋላ ወደ ሎተሪ ድርጅቱ ያመራል።
ይሁን እንጂ ቺክስ ትኬቱን ለሎተሪ ቢሮው ሲያቀርብ ህይወቴን ይቀይራል ያለው ወረቀት (340 ሚሊየን ዶላር የሚያስገኝ) “ጥቅም የሌለውና ቆሻሻ ውስጥ መጣል ያለበት ነው” የሚል ምላሽ ተሰጠው።
የጃክፖት አሸናፊ መሆኑን ድረገጽ ላይ ከወጣው የአሸናፊ ቁጥር ጋር እያመሳከረ ለማስረዳት ቢሞክርም ሊቀበሉት አልቻሉም።
ቺክስ የነበረው አማራጭ ወደ ገንዘብ ያልተለወጠውን ትኬት ይዞ ጠበቃ መፈለግ ነበር።
በቅርቡም ደስታየን አጨልመዋል ያላቸውን ፓወርቦል እና ዲሲ ሎተሪ መክሰሱን ነው ቢቢሲ የዘገበው።
ፖወርቦል የተሰኘው የሎተሪ ድርጅት እና የእጣ አወጣጡን የሚያካሂደው በዲሲ የሚገኘው ታኦቲ ኢንተርፕራይዝ “ስህተቱ” የተፈጠረው በቴክኒክ ችግር ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ጆን ቺክስ ባለፈው አመት (ጥር 6 2023) ትኬቱን ሲገዛ የእጣ አወጣጡን ጥራት የሚያረጋግጥ ቡድን በድረገጹ ላይ ሙከራ እያደረገ ነበር ሲልም አንድ የታኦቲ ኢንተርፕራይዝ ሰራተኛ ለፍርድ ቤት ማስረዳቱም ተመላክቷል።
በእለቱም ከቺክስ የፓወርቦል ትኬት ቁጥሮች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ቁጥሮች በ”ድንገት” ድረገጹ ላይ መለጠፋቸውና ለሶስት ቀናት ድረገጹ ላይ መቆየታቸውም ነው የተገለጸው።
በድረገጽ ላይ የተለጠፉት ቁጥሮች (ጆን ቺክስን የ340 ሚሊየን ዶላር አሸናፊ ያደረጉት) በሌላ ቀን ከወጣው የመጨረሻና ትክክለኛ እጣ ጋር ተመሳሳይ አለመሆናቸውን በመጥቀስም “በስህተት” ተፈጥሯል ስለተባለው ጉዳይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ይሁን እንጂ የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪውን ጆን ቺክስ እነዚህ ሁሉ መረጃዎች ሊያሳምኑት አልቻሉም፤ “ስምምነትን በመጣስ፣ በእንዝህላልነት፣ በማጭበርበርና የስሜት ስብራት በማድረስ በሚሉና ሌሎች ስምንት ክሶች መስርቷል።
ጠበቃው ሪቻርድ ኢቫንስም ጉዳዩ የሎተሪ ኩባንያዎችን ተአማኒነት እና ተጠያቂነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑን በመጥቀስ “የጃክፖት አሸናፊው ደንበኛየ 340 ሚሊየን ዶላር ሊከፈለው ይገባል” ብሏል።
እጣው የወጣው በስህተት ነው ከተባለም ለደረሰበት ከፍተኛ የሞራል ስብራት የሚመጥን ካሳ እንዲከፈለውም ጠይቋል።