የጽዳት ሰራተኞቹ አዋጥተው በገዙት ቲኬት የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ አሸነፉ
ሰራተኞቹ "እድሜ ልካችንን በድህነት ነበር የኖርነው፤ አሁን ሊያልፍልን ነው" ብለዋል
የጽዳት ስራቸውን ከመተው ይልቅ ድካም በሚቀንስ መልኩ መስራታችንን እንደሚቀጥሉምገልጸዋል
የጽዳት ሰራተኞቹ አዋጥተው በገዙት የሎተሪ ትኬት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር አሸነፉ፡፡
ከሰሞኑ በሕንዷ ክራላ ግዛት ነዋሪው ሁሉ ደስታ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዚች ግዛት ስራ ባለችው ፓራፓናንጋዲ ከተማ ህይወታቸውን በድህነት የሚመሩ ሴቶች ሎተሪ ስለደረሳቸው ነው፡፡
እነዚህ ዜጎች በሕንድ ዳሊት በተለምዶ አይነኬ የሚል የዘር ሀረግ ያላቸው በመሆኑ በመገለል እና በሌሎች ምክንያቶች ህይወታቸውን በድህነት የሚመሩ ናቸው ተብሏል፡፡
በከተማዋ በጽዳት ስራ የሚተዳደሩት እነዚህ 11 ሴቶች ስራቸውን እየሰሩ እያለ አንድ ሎተሪ አዟሪ ጠጋ ብሎ ሎተሪ ግዙኝ ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡
ሴቶቹም የአንድ ሎተሪ ዋጋ 250 ሩፒ ወይም 5 ዶላር መሆኑ አቅማቸውን መፈታተኑን ተከትሎ ለምን አዋጥተን አንድ የሎተሪ ቲኬት አንገዛም ሲሉ ይነጋገራሉ፡፡
ለየብቻ አንድ ሎተሪ ቲኬት መግዛት ያልቻሉት እነዚህ ህንዳዊያን ለ11 ሆነው አንድ ሎተሪ ቲኬት ለመግዛት ይስማማሉ፡፡
ይሁንና ከመካከላቸው አንዷ 25 ሩፒ ማዋጣት እንደሚከብዳት መናገሯን ተከትሎ ውጥናቸው እንዳሰቡት ሳይሆን ይቀራል።
ይሁን እንጂ ውስጣቸው አንዳች ነገር ሹክ ስላላቸው ገንዘቡ የለኝም ያለችው የስራ ባልደረባቸውን ከማግለል ይልቅ የእሷን ድርሻ ለ10 በመካፈል አዋጥተው ይሸፍኑላታል።
በመጨረሻም እነዚህ ድሃ ሕንዳዊያን ለ11 በቆረጡት አንድ የሎተሪ ቲኬት 100 ሚሊዮን ሩፒ ወይም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ ማሸነፋቸው ተገልጿል፡፡
እነዚህ ሴቶች እያገኙ ካለው ወርሃዊ ደመወዝ አንጻር ያሸነፉት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ የሚባል ሲሆን ሕይወታቸው እንደሚቀየር በመናገር ላይ ናቸው፡፡
የጽዳት ስራችንን አንተውም የሚሉት እነዚህ እድለኞች እያንዳንዳቸው 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሩፒ አልያም 76 ሺህ ዶላር ይደርሳቸዋል የተባለ ሲሆን ስራችንን ድካም በሚቀንስ እና የተሸለ ገቢ በሚያስገኝ መልኩ እናስኬዳለን ማለታቸውን ዘጋርዲያን አስነብቧል።
"ሎተሪው የደረሰን ጌታ የእስካሁኑ የስቃይ እና የድካም ህይወታችሁ ይበቃል ስላለ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡