በዘንድሮው የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የትኛው ተጫዋች የበለጠ ይደምቅ ይሆን?
በአህጉሩ ውድድር ላይ ለግብጽ 13 ጊዜ የተሰለፈው መሀመድ ሳላህ የዘንድሮው የመጨረሻው ውድድር ሊሆን ይችላል ተብሏል
34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ20 ቀናት በኋላ በኮቲዲቯር አዘጋጅነት ይካሄዳል
በዘንድሮው የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የትኛው ተጫዋች የበለጠ ይደምቅ ይሆን?
34ኛው የአፍሪካ ወንዶች አግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ከጥር 4 እስከ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ይደምቃሉ ተብለው ከተለዩ ተጫዋቾች መካከል ግብጻዊው እና የሊቨርፑል የፊት መስመር ተጫዋች መሀመድ ሳላህ ዋነኛው ነው፡፡
ተጫዋቹ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሩን ሲወክል ለ14ኛ ጊዜ ሲሆን የመጨረሻው ውድድር ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
መሀመድ ሳላህ ሀገሩን በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ላይ በአሳዛኝ ሁኔታ ማሳለፍ ካለመቻሉ ባለፈ ከሁለት ዓመት በፊት በካሜሩን በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ዋንጫውን ማሳካት ሳይችል ቀርቷል፡፡
በነዚህ ምክንያቶች በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ለዋንጫ ተጠባቂው ሲሆን የ31 ዓመቱ መሀመድ ሳላህም ኮኮብ ግብ አግቢ ሆኖ ሊያጠናቅቅ ይችላል ተብሏል፡፡
ሌላኛው በዚህ ውድድር ላይ ይደምቃል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች ናይጀሪያዊው እና የናፖሊው አጥቂ ቪክተር ኦስሜን ነው፡፡
ለ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት
የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተቻዋች ሽልማትን ያሸነፈው የ24 ዓመቱ ኦስሜን በዘንድሮው ውድድር ላይ እንደሚደምቅ እና ሀገሩንም ለዋንጫ ያበቃል ተብሎ ተጠብቋል፡፡
ተጨዋቹ በአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን ወክሎ ይጫወታል የተባለ ሲሆን ናይጀሪያ ከውድድሩ አዘጋጅ ኮቲዲቯር እና ሌላኛዋ ተፎካካሪ ኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ያለባትን ጨዋታ በድል የማጠናቀቅ ሃላፊነትም ተጥሎበታል፡፡
በጥር የዝውውር መስኮት ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሊዛወር ይችላል የተባለው ኦስሜን በአፍሪካ ዋንጫ የሚያሳየው ብቃት በተፈላጊነቱ ላይ አስተዋጽኦ ሊያደርግለት እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ሌላኛው የዚህ ውድድር ተጠባቂ ተጫዋች የጊኒው እና የስቱት ጋርቱ ሰርሁ ጉራሲ ሲሆን በተለይም በ10 የቡድንስሊጋ ጨዋታዎች ላይ 15 ጎሎችን ማስቆጠሩ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ከምድቧ ማለፍ ሳትችል ቀርታ በጊዜ የተሰናበተችው ጋና በዘንድሮው ውድድር ላይ ለዋንጫ ከሚጠበቁ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዷ ሆናለች፡፡
ለዌስትሀም ዩናይትድ የሚጫወተው ሞሃመድ ኩዱስ በዚህ ውድድር ላይ ተጠባቂው ተጫዋች ሲሆን ተጫዋቹ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ ጎል የማስቆጠር ፍጥነቱ ከፍተኛ ነውም ተብሏል፡፡
የቡርኪናፋሶው ኢሳ ካቦሬ እና የሞሮኮው አዘዲን ኦናሂ በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይደምቃሉ ተብለው ከተለዩ ተጫዋቾች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የውድድሩ ባለቤት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ውድድሩን የሚዳኙ ከ32 ሀገራት የተውጣጡ ዳኞችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን የተንቀሳቃሽ ምስል ዳኝነት ወይም ቫርን ጨምሮ 68 ዳኞችን ይፋ አድርጓል፡፡