ከ20 ቀን በኋላ ለሚጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ባምላክ ተሰማን ጨምሮ የ68 ዳኞች ዝርዝር ይፋ ሆኗል
የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ በኮቲዲቯር አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ በዳኝነት ብቻ ትሳተፋለች
ኢትዮጵያ ለዚህ ውድድር አንድ ዳኛ ብቻ ስታስመርጥ ግብጽ እና ሞሮኮ ሰባት ሰባት ዳኞችን አስመርጠዋል
ከ20 ቀን በኋላ ለሚጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ባምላክ ተሰማን ጨምሮ የ68 ዳኞች ዝርዝር ይፋ ሆኗል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኮቲዲቯር አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን ውድድሩ ከጥር 4 እስከ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
የውድድሩ ባለቤት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩን የሚዳኙ ከ32 ሀገራት የተውጣጡ ዳኞችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን የተንቀሳቃሽ ምስል ዳኝነት ወይም ቫርን ጨምሮ 68 ዳኞችን ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያዊው ባምላክ ተሰማ ውድድሩን እንዲመሩ ከተመረጡ ዳኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ብቸኛው ሆነዋል፡፡
ጎረቤት ሀገር ኬንያ ሶስት ዳኞችን ስታስመርጥ ሱዳን ሁለት ሲያስመርጡ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ደግሞ አንድ ዳኛ ብቻ ማስመረጥ ችለዋል፡፡
በአጠቃላይ ለውድድሩ ከተመረጡ 68 ዳኞች መካከልም ስድስቱ ዳኞች ሴቶች እንደሆኑም ካፍ በድረገጹ አስታውቋል፡፡
አልጀሪያ አምስት፣ ግብጽ ሰባት፣ ሞሮኮ ሰባት፣ ጋቦን፣ ኮቲዲቯር፣ ሴኔጋል እና ኬንያ እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ዳኞችን አስመርጠዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በ2021 የተካሄደውን ውድድር ካሜሩን አዘጋጅታው ሴኔጋል ዋንጫውን ስትበላ ግብጽ ሁለተኛ አዘጋጇ ካሜሩን ሶስተኛ እንዲሁም ቡርኪናፋሶ ደግሞ አራተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡
ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የ2013 አፍሪካ ዋንጫ ላይ ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ መሳተፏ አይዘነጋም፡፡